Monday, July 16, 2012

ምሽግ ቆፋሪዎች



እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት ከጦርነት ጋር ኖረናል፡፡ ሀገራችንን ከባዕዳን ጠብቀን ሀገረ አግዓዝያን ለማድረግ የመጡብንን ከመከላከል የተሻለ አማራጭ አልነበረንም፡፡

ሽፍቶች ከሽፍቶች፣ ዐማፅያን ከመንግሥት፣ መንግሥት ከዐማፅያን ስንዋጋ ኖረናል፡፡ እኛም በኩራት «ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን ጦርነትን መሥራትም እንችልበታለን» እያልን እስከ መናገር ደርሰናል፡፡
ታሪካችን ሲመዘዝ ማጉ ነፃነት ቢሆንም ድሩ ግን ጦርነት ሆኖ ይገኛል፡፡ የምንዋጋው ጠላት ባይኖረን እንኳን በሰላም ወደሚኖሩት አራዊት መንደር ብቅ ብለን ዝሆን እና አንበሳ፣ አጋዝን እና ነብር ገድለን በመምጣት እንፎክራለን፡፡ የባሰ ሰላም ካጋጠመን ደግሞ ጦር አውርድ ብለን እንጸልያለን እያሉ አንዳንድ የቀድሞ ድርሳናት ያወጉናል፡፡
ታድያ ይህ በጦርነት አድገን በጦርነት መኖራችን በአንድ በኩል ጀግና እና አልደፈር ባይ፣ ዘመናዊ ጦር ታጥቀው የመጡትን በባህላዊ ቆራጥነት እና በሀገር ፍቅር ወኔ የሚገዳደር እና የሚያሸንፍ ሕዝብ ሲያፈ ራልን፣ በአንድ በኩል ደግሞ የራሱን ጠባሳ ጥሎልናል፡፡ መቼም አንከን የሌለው መድኃኒት አይፈጠርም፡፡

ኢትዮጵያን የነፃነት ሀገር ያደረጋት ከሕዝቦቿ ቆራጥነት በተጨማሪ የመልክዐ ምድሯ ቆራጥነትም ጭምር ነው፡፡ እዚያው ተወልዶ እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል ሲወጣ ሲወርድ ላላደገ ሰው ምድሪቱ አስቸጋሪ ናት፡፡ ሐበሻ ምድርን መምረጥ፣ ምሽግ መቆፈር እና መከላከል፣ ከዚያም ማጥቃት ያውቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ ሕይወታችንን የምሽግ ሕይወት አድርጎታል፡፡
ቀደምት ከተሞቻችን ለምሽግ እንዲያመች ዙርያውን በተራራ በተከበበ ቦታ ወይንም ደግሞ ራሳቸው በተራራ ላይ የተገነቡ ናቸው፡፡ ቤተ መንግሥቶቻችን ለምሽግ በሚያመች መንገድ የተሠሩ ናቸው፡፡ ይህ ባህላችን እስከ ቅርቡ የጦርነት ታሪካችን ዘልቆ ኢሕአዴግ ሲገባም በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ምሽጎች ተሠርተው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የድንጋይ ምሽጎችም በቅርስነት ዛሬም ከ19 ዓመታት በኋላ ይታያሉ፡፡
ከቤቱ ይልቅ ለግቢው ጥንካሬ የምንጨነቀው ይኼው የምሽግ ባህል ይዞን መሆን አለበት፡፡ ጠንከር እና ከፍ ያለ ማንንም የማያሳይ ግቢ የትልቅ ሰው ግቢ ይባላል፡፡ ከምድር ወደ ፎቅ ስንወጣም ይኼው ተከተለንና በየኮንደሚኒየሙ ምሽጎችን እናያለን፡፡ በተለይም የሕንፃውን ጥግ ማግኘት የቻሉ ወገኖቻችን በተቻላቸው መጠን በረንዳውን አጥረው አንበሳ ግቢ ያስመስሉታል፡፡ ዕረፍት የሚሰማቸው እና ርካታ የሚያገኙት ምሽግ ሲኖራቸው ነውና፡፡
በየአዳሪ ትምህርት ቤቱ ብትገቡ እልፍ አእላፋት ምሽጎችን ታያላችሁ፡፡ በአንድ ክፍል አሥር እና አሥራ አምስት ሆነው የሚኖሩ ተማሪዎች የሚመሽጉት ቢያጡ አልጋቸውን ይመሽጋሉ፡፡ ዙርያዋን በአንሶላ ወይንም በጋቢ ያጥሯታል፡፡ እንደ ቀበሮ በር የጠበበች መግቢያም ያበጁላታል፡፡ ያን ጊዜ መንፈሳቸው ደኅንነት ይሰማዋል፡፡ ነፍሳቸውም ዕረፍትን ታገኛለች፡፡
ሂዱ ደግሞ በየቢሮው፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ የየራሱን በግንብ የታጠረ ቢሮ ካላገኘ እንደተበደለ አድርጎ ነው የሚቆጥረው፡፡ ቆልፎ የሚቀመጥበት፣ ቢቻል የብረት በር ያለው ቢሮ ማግኘት መታደል ነው፡፡
እዚህ አዲስ አበባ በአንድ አዲስ ሕንፃ ውስጥ መሐንዲሶቹ እስከ ወገቡ ኮምፔልሳቶ ከወገቡ በላይ ደግሞ መስተዋት የሆነ ቢሮ እንዲሠራ ያደርጋሉ፡፡ በየቢሮው የተመደቡት ሠራተኞች ቢሮውን መረከብ በጀመሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ መስተዋቶቹ ሁሉ በሰፋፊ ጋዜጦች ተሸፈኑና የካራማራን ምሽግ መስለው ቁጭ አሉ፡፡ ጭራሽ ይባስ ብለው ኃላፊዎቹ ቢሮውን ሲረከቡ ደግሞ «አንዲህ ያለው አሠራር ለደኅንነታችን አያመቸም» አሉና መስተዋቱን አስነቅለው በኮምፔልሳቶ ጠረቀሙትና መሽገው ቁጭ አሉ፡፡
ለደንበኞች ቅርብ የሆኑ ሠራተኞች በቀላሉ ከደንበኞቻቸው ጋር እየተያዩ እንዲሠሩ ተብሎ በየመሥሪያ ቤቱ የመስተዋት ቢሮዎች እየተገነቡ መጥተዋል፡፡ በሠራተኞቹ ኅሊና ውስጥ ያለው የምሽግ ቆፋሪነት ባህል ስላልለቀቀን ግን በተቻለ መጠን በካርቶን፣ በጋዜጣ፣ በመጋረጃ እና ሠልጠን ያሉት ደግሞ በትልልቅ ሥዕሎች መስተዋቱ እንዲሸፈን ይደረጋል፡፡ ምናልባትም ከሁለት ዓመት በኋላ ብንሄድ መስተዋቶቹ ተሰባብረው በላሜራ እና በኮምፔልሳቶ ተተክተው መስተዋቱ «ነበር» ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ስብሰባ ወይንም ጉባኤ ተጠርቶ ሰው ወደ አዳራሽ ሲገባ እስኪ ተመልከቱ፡፡ ሁሉም ጥግ ጥጉን እየፈለገ መቀመጥ ይጀምራል፡፡ ወደ መሐል እና ወደ ፊት ተሰብሳቢዎቹን ለማምጣት ፕሮግራም የሚመሩት አካላት መለመን ወይንም ማስነሣት አለባቸው፡፡ ምን ስብሰባ ላይ ብቻ፡፡ ሻሂ ቤት እና ምግብ ቤት ብትገቡ ብዙ ጊዜ በመካከል ላይ ያሉ ወንበር እና ጠረጲዛዎች ባዶዎች ናቸው፡፡ እንግዶቹ ሁሉ ወደ ግድግዳው ጥግ እየሄዱ ምሽግ ምሽግ ይዘው ታገኟቸዋላችሁ፡፡
­ጥግ፣ ማዕዘን፣ ሥርቻ፣ ሠወር ያለ ቦታ፣ ከለላ፣ መያዝ የብልህነት ማሳያ ተደርጎም ይታያል፡፡ ምንም ያህል ሰፊ ቦታ በመካከል ቢኖርም አልጋችን ግን ጥግ መያዝ አለበት፡፡ ሶፋው ወንበር ጥግ ከተቻለም የግድግዳው መዓዝን ላይ መቀመጥ አለበት፡፡ ስንበላ ጥግ ይዘን፣ ስንሸና ጥግ ይዘን፣ ስናማ ጥግ ይዘን፣ ስንተኛ ጥግ ይዘን፣ ስንተኩስ ጥግ ይዘን፡፡ ምሽግ ቆፋሪዎች፡፡
በየክርክሩ፣ በየስብሰባው፣ በየውይይቱ፣ እያንዳንዳችን በየምሽጋችን ሆነን መተኮስ እና መከላከል እንጂ ወደ መካከለኛ ቦታ መምጣት የማንፈልገው በዚሁ ልማዳችን ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሁሉም ጥጉን ይዞ፣ ጥጉን አስከብሮ ለመቀጠል እንጂ ሁሉን ሊያግባባ ወደሚችል መካከለኛ ሃሳብ ለመምጣት ፈቃደኛነት የማናሳየው በዚህ የምሽግ ቆፋሪነት ባህል ውስጥ ሆነን ስለምንነጋገር ይመስለኛል፡፡
ነጥብ ማስቆጠር፣ በዝረራ መጣል፣ አንገት ማስደፋት፣ ልክ ልኩን መንገር፣ ውሻ በጨው እንዳይልሰው አድርጎ ማዋረድ፣ አንገቱን መሰባበር፣ ማቅመስ እና ጥንብ እርኩስ ማውጣት የሚሉት አገላለጦቻችን ከመሐል ሜዳ የሚመነጩ ሳይሆኑ ከምሽግ ውስጥ የሚወጡ ናቸው፡፡
ድንበራውያን እንስሳት /territorial animals/ የሚባሉ አሉ፡፡ እንደ አንበሳ፣ ነብር፣ ተኩላ ያሉ ናቸው፡፡ የእነርሱን የመኖርያ ክልል በጠረናቸው ያጥሩታል፡፡ ሌላ እንስሳ ያችን የጠረን ድንበር ተሻግሮ ሊገባ አይችልም፡፡ እርሱም ጠረኑን አሽትቶ ይሸሻል፤ ከገባም እርም እንዲል አድርገው ዋጋውን ይሰጡታል፡፡
እኛ ከእነርሱ እንቅሰመው ወይንም እነርሱ ከኛ ይቅሰሙት አላወቅም እንጂ ይህ ድንበርተኛነት እኛም ጋ ይታያል፡፡ በራስ ባህል፣ ልማድ፣ ቋንቋ፣ ጎጥ፣ ጎሳ፣ አስተሳሰብ፣ እምነት እና አሠራር ብቻ ታጥሮ መኖር፡፡ ሌላ ቦታስ ምን ሊኖር ይችላል? ብሎ አለመገመት፡፡ ከጎሳ ውጭ ማግባት ዛሬም ለብዙዎች ይከብዳል፡፡ ከ88 በላይ ቋንቋ በሚነገርባት ሀገር ብዙዎቻቸን ከራሳችን ቋንቋ ውጭ አልተማርንም፣ እንድንማርም አልተደረገም፡፡
በምሁሮቻችን ዘንድ እንኳን አንዱ ምሁር ስፔሻላይዝ አድርጎ ታዋቂ በሆነበት የዕወቀት መስክ ሌላው እንዳይከተለው ወይንም እንዳይቀላቀለው አጥሮ ነው የሚቀመጠው፡፡ እርሱ ብቻ ሊቅ፣ እርሱ ብቻ ተጠያቂ፣ እርሱ ብቻ ዐዋቂ መሆንን እንደ ልዩ ክብር ያየዋል፡፡ እርሱም ከምሽግ አይወጣ፣ ሌላም ወደ ምሽግ አያስገባ፡፡ እርሱ በሄደበት ሌላው እንዳይሄድ ዱካውን አጥፍቶ፣ መንገዱን ዘግቶ፣ ድልድዩን አፍርሶ፣ መረጃውን ደባብቆ ቁጭ ይላል፡፡
አብዛኞቹ ነጋድያኑም ቢሆኑ በዚያው በምሽግ ቆፋሪነት ባህል ውስጥ ነው ያሉት፡፡ አንድ ዕቃ ያመጣል፡፡ ያመጣበትን አይናገርም፡፡ ብቸኛ ወኪል አድርጉኝ ይላል፤ የሌሎች ዕቃ ከጉምሩክ እንዳይወጣ ጉቦ ሰጥቶም ቢሆን እንዲዘገይ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አንድ ምሽግ ውስጥ ቁጭ ብሎ ይቸበችባል፡፡
ይህ ልማድ ወደ ታች ወርዶ ወርዶ በየሠፈሩ ዕቃ ከሚያወርዱ እና ከሚጭኑ ወጣቶች ዘንድ በመድረሱ በእነርሱ ሠፈር እነርሱን አልፎ ማንም እንዳያወርድ እና አንዳይጭን የተወካዮች ምክር ቤት ያላወቀው ሕግ ደንግገዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መከራከር፣ መነጋገር፣ እምቢ ማለትም አይቻልም፡፡ በእነርሱ ሃሳብ እና ዋጋ መስማማት ግዴታ ነው፡፡ ያ አካባቢ በእነርሱ የሥልጣን ጠረን የታጠረ ክልላቸው ነው፡፡
በእምነት ተቋማትም ዘንድ ይህ የምሽግ ቆፋሪነት ባህል አለ፡፡ በየምሽጉ ሆኖ መታኮስ እንጂ ችግሮችን ተወያይቶ እና ተመካክሮ ለመፍታት ወደ መካከል የሚመጣ የለም፡፡ አሸናፊ እና ተሸናፊን ለመለየት እንጂ በየአመንንበት መንገድ እየሄድን ሌላውን ሳንነካ እና ሳንጋጭ እንዴት መኖር እንደሚቻል ለመነጋገር ወደ ሜዳ የሚመጣ የለም፡፡ ሁሉም በየምሽጉ ነው፡፡ ግዳይ መጣጣል፣ የጠላትን ምሽግ መሰባበር፣ መማረክ እና ድል ማድረግ ብቻ ነው የሚታየን፡፡
ዲያስጶራውም እንዲሁ በየምሽጉ ነው የሚኖረው፡፡ ጎንደሬው፣ ጎጃሜው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ ሸዋው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ሶማልያው በየክልሉ መሽጎ ድንበር ይጠብቃል፡፡ ምሽግ ያጠናክራል፡፡ በየሬዲዮ ጣቢያው፣ በየድረ ገጹ፣ በየጋዜጣው፣ በየሰላማዊ ሰልፉ፣ በየስብሰባው ይህንኑ የምሽግ ቁፋሮውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አይገናኝም ይታኮሳል፤ አይከራከርም፣ ያነጣጥራል፣ አይወያይም፣ ይከላከላል፡፡ ከእርሱ ድንበር ውጭ ያለው የዓለም መጨረሻ ነው፡፡
አሁን ወደ መሐል የሚመጣ እና የሚያመጣ ያስፈልጋል፡፡ በየምሽጋችን ተቀምጠን ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ልናኖራት አንችልም፡፡ ምሽግ ለጦርነት እንጂ ለሰላማዊ የዕድገት ጉዞ አይፈይድም፡፡ ገና ከጦርነት አስተሳሰብ የወጣን አንመስልምኮ፡፡ አሁንም በማጥቃት እና መከላከል መርሕ በመጓዝ ላይ ነንኮ፡፡
እባካችሁ ከየምሽጋችን እንውጣ፡፡
ወደ መሐልም እንምጣ፡፡
ዳንኤል ክብረትhttp://www.danielkibret.com/

1 comment:

  1. THIS IS AN EXCELLENT OBSERVATION HAVING SAID THAT I DON'T COMPLETELY AGREE WITH THE BEGGING PREMISES WE ALL ARE TERRITORIAL ANIMALS ITS OUR NATURE ... BUT I LIKE HIS MESSAGE IN THAT WE SHOULD INDEED COME TOGETHER AND HELP EACH OTHER INSTEAD OF HINDERING EACH OTHER.

    ReplyDelete