በግደይ
ገብረኪዳን
በዘመናዊው የሰውልጆች ታሪክ የሚስጥር ማህበራት ተፅእኖ ላይ በሚደረገው ጥናት
ኢሉሚናቲ የተባለው የሚስጥር ማህበር ሰፊ ድርሻ ይይዛል፡፡ ኢሉሚናቲ ምንድን ነው፣ የእውን ዓለምን ይገዛል? ወይስ አፈ ታክ
ነው? ይህን ማወቅ የሚሹ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የሚገኘው መረጃም ሙሉ ባልሆኑ ምርምሮችና በሚለቀቁ ማሳሳቻ
መረጃዎች ሳቢያ ምላሹን ከባድ አድርጎታል፡፡ በዚህ ክፍልም ይህን ለመመለስ ይሞከራል፡፡
ኢሉሚናቲ እና ፍሪሜሶኖች አንድ ናቸው? ግባቸው ምንድን
ነው? እምነታቸው ምንድን ነው? በሚስጥር የሚንቀሳቀሱት ለምድን ነው? ባእድ አምልኮ ይከተላሉ? ይህን ሁላ ጥያቄዎች መመለስ
ከባድ ስራ ነው፡፡ አጥጋቢ ሰነድና ያለመኖርና አሳሳች መረጃ መለቀቅ የዚህ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የሚስጥር ማህበራት የሚስጥር
እንደመሆናው እና ታሪክ የሚፃፈው ደሞ ባሸናፊዎች እንደመሆኑ ይህ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው፡፡ በኢሉሚናቲ ዙርያ የተፃፉት አንድአንድ
ሰነዶች በራሳቸው በሚስጥር ማህበራቱ አባሎች ማለትም እንቅስቃሴውን ወደ ፊት ሲያስኬድ የሚችለውን ፍልስፍናዊና መንፈሳዊ ሞገድ
ሊረዱ በሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በመጠቀም መነሻዎቹን፣ አካሄድ ዘዴውን እና በአለም ታክ ላይ የተወውን አሻራ
እንዳስሳለን፡፡
ከቀደምት ግዝያት ጀምሮ የተለያዩ ቡድኖች እራሳቸውን ኢሉሚናቲ እያሉ ቢጠሩም በታሪክ
የማይረሳውና ሰፊ ተፅእኖ የፈጠረው የባቫርያው ኢሉሚናቲ ነው፡፡ በ 1 ግንቦት (ሜይ 1) 1976 ዓ.ም በአዳም ዉሻፕት
የተመሰረተው ይህ ማህበር በመንፈሳዊና ፖለቲካዊ የሚስጥር ማህበራት የነበረውን ልዮነት የደመሰሰ ነበር፡፡ የፍሪሜሶኖችንና
የሮዚክሩሽያኖችን የባእድ ሳይንሶችን በመቀላቀል በሌላ እጅ በዝርዝር የተቀመጡ ፖለቲካዊ ግቦችን ለማሳካት በማሴር ኢሉሚናቲ
በዓለም መድረክ ዋና ተዋናይ ሆነ፡፡ በግዜው የነበሩ የሚስጥር ማህበሮች ከባእድ እውቀቶችና ሃብታም ሰዎች ዙርያ ሲያንዣብቡ
የባቫርያ ኢሉሚናቲ ዓለምን ለመቀየር በትጋት ይሰራ ነበር፡፡
የሚስጥር ማህበራት በታሪክ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ዓላማዎች ይዘው ተነስተዋል፡፡
የጥንታዊ ግብፅ የሚስጥራት ትምህርት ቤቶች የግብፅ አስተዳደራዊ ተቋም አካላት ነበሩ፤ ሌሎች ቡድኖች በአመፅ አላማቸውና
ሴረኝነታቸው ሳቢያ ሚስጥራዊ ነበሩ፡፡ የመጀመርያው የመንፈሳዊ ገፅታ ሲሆን ሁለተኛው ፖለቲካዊ ገፅታውን የሚያሳይ ነው፡፡
የባቫርያ ኢሉሚናቲ በሁለቱም መስመሮች የሚንቀሳቀስ ነበር፡፡
“መንፈሳዊ
ወንድማማችነት ቃል የሚገቡት ለጥበብና የሰው ልጆችን መጨረሻ ወደሌለው አካል ለመምራ ነው፤ ፖለቲካዊ ወንድማማችነት የሚያካትቱት
የማታለያ አጀንዳቸውን በጭለማ የሚጋርዱ ስልጣን ፈላጊዎች ስብስብ ነው፡፡
ሁሉም የሚስጥር
ማህበራት አንድ የሚያደርጋው ነገር አለ፡፡ አባልነት በጉዳዩ ፍላጎት ላላቸው ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ እናም መንፈሳዊ ቡድን የዛን
አይነት አስተማሪ ወይም አካሄድ የበለጠ እውቀት የሚሹትን ይስባሉ፡፡ ተማሪው ጉዳዩን አስቀድሞ የሚያውቅና በዛ ዙርያ የበለጠ
እውቀት የሚሻ ከሆነ ቡድኑን ቀርቦ ያነጋግራል፡፡ አልፎ አልፎ ደሞ ለዓላማው መቀራረብ አለው ለተባለ ግለሰብ ቡድኑ ጥሪ
ሊያደርግለት ይችላል፡፡ …
በፖለቲካዊ
የሚስጥር ማህበር ቡድኑ የሚወክላቸው ርእዮተ ዓለሞች ጋር ለሚስማሙ ብቻ የተገደበ ነው፡፡ ከፖለቲካዊ አድማሱ የመጨረሻው እይታ
አብዮት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ማህበር ራሱን ለመከላከል አርቆ ይጓዛል፡፡ …
ኢሉሚናቲዎች
በመንፈሳዊና ፖለቲካዊ የሚስጥር ማህበራት ያለውን ልዩነት የደመሰሱ ናቸው፡፡ ብዙውን ግዜም የ1787 የፈረንሳይ አብዮትን
በማካሄድ የሚወደሱ (ወይም የሚወቀሱ) ናቸው፡፡ ኢሉሚናቲዎች በሰው እኩልነት፣ አመክንዮታዊነትን (ራሽናሊዝም) መቀበል፣ የማህበራዊና
ሞራል እሴቶችን የሚያፀድቁ ዘውድና ቤተ ክርስትያን መሆናቸውን አለመቀበል የሚያስተምሩ የፖለቲካዊና ማህበራዊ ነፃነት
ዶክትሪኖችን ያስተምሩ ነበር፡፡ … የኢሉሚናቲ ሃሳቦች ከግዜው ወጣ ያሉ ቢመስሉም መነሳሷቸው አብዮቶች ግን ወደ አሰቃቂ የደም
መፋሰስና የነበረው የሞራል አቅጣጫ መሳት የሚዘገንን ነበር፡፡ (James Wasserman, The Mystery Traditions)
አንዳንዶች የኢሉሚናቲ ብቸኛ ፈጣሪ አዳም ዉሻፕት ነው፣ ኢሉሚናቲም ገናናነትን
ለማግኘትና ለመጥፋት የ12 ዓመታት እድሜ ብቻ ነበረው ብለው ቢናገሩም አብዛኞቹ የባእድ ሚስጥራቱን የሚያቁ አባሎች እንደሚፅፉት
ግን የባቫርያ ኢሉሚናቲ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ወንድማማችነት መገለጫና መሰረቱም እስከ መካከለኛው ዘመን የነበሩት ናይትስ
ቴምፕላርስ (የቤተመቅደሱ ባለሟሎች) ድረስ የሚሄድ እንደሆነ ይፅፋሉ፡፡
ማንሊ ፒ. ሃል 33ኛ መዓርግ የደረሰ ሰፊ ተቀባይነት ያለው
የራሳቸው የፍሪሜሶኖች ፀሃፊ “Masonic Orders of Fraternity” በሚል ፅሁፉ ለዘመናት ሳይታይ ለለውጥ ሲሰራ የነበረ “የማይታየው ግዛት” ስለሚለው ነገር
ያብራራል፡፡ በታሪክ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያየ ስም በያዙ የተለያዩ ድርጅቶች አንዳንዴ ይታያል ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው
እኚህ ቡድኖች የማይታወቅ ግን ታላቅ ተፅእኖ በማህበረሰቡ ላይ ፈጥረዋል ይላል፡፡ ይህም ቀጣዩን ትውልድ ለመቅረፅ የትምህርት
ስርአቱን በመቀየርም ሳይቀር ይላል፡፡ በዚህ ፅሁፉ ሃል በ17ኛው እና በ18ኛ ክ/ዘመን የባቫርያ ኢሉሚናቲ በንቃት
በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚስጥር ማህበራትን ስራ በተመለከተ “ዝምታና” የመረጃ እጥት እንደነበር ይገልፃል፡፡ በዚህ ግዜ ነው
የሚስጥር ማህበራት አብዮቶችን በማስነሳት፣ ዘውዳዊና ሃይማኖታዊ ስልጣናትን በማናጋት ስራና የባንክ ስርአቱን በመቆጣጠር
እንቅስቃሴዎች ተወጥረው የነበሩት፡፡ የባቫርያ ኢሉሚናቲ ሃል የሚለው የማይታየው ግዛት አካል ነበር? ዛሬስ እየተንቀሳቀሰ ነው
ወይስ ጠፍቷል? መጀመርያ አዳም ዉሻፕትንና አሳፋሪ የሚስጥር ማህበሩን እንመለከታለን፡፡
አዳም
ዉሻፕት
በኢንጎልስታድት፣
ባቫርያ በጥቅምት 6፣ 1748 ዓ.ም ተወለደ፡፡ አባቱ ሰባት ዓመቱ እያለ ሞተበት፣ የክርስትና አባቱ ባሮን እክስታት
አንዲያስተምሩለት በወቅቱ ሃያል ለነበሩት ለጀስዊቶች (የሱሳውያን) ሰጣቸው፡፡ ጀስዊት ካቶሊኮች የእምነታውን ደህንነት
(በእውቀትም በጉልበትም) ለማስጠበቅ የመሰረቱት ማህበር ነው፡፡ በአመፃ ተግባራት፣ በማሴር የሚታወቀው ማህበር በባቫርያ
ፖለቲካና ትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ይዞታ ነበረው፡፡
የዚህ
የካቶሊኮቹ የሱሳውያን ማህበር ውስጣዊ አሰራር ሲዋጋቸው ከነበሩ የባእድ ወንድማማቾች አሰራር ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ መዓርጎች
ነበሩት፣ ሚስጥር የሚነገሩበት ስነ ስርአቶች፣ ጥንታዊ ምልክቶች ነበሩት፣ በተጨማሪም በተለያዩ አገሮች በአመፃ ስራዎቹ በተለያዩ
ግዝያት እገዳ ተጥሎበት ያውቃል፡፡
በ1773
የዉሻፕት ክርስትና አባት በኢንጎልስታድት ዩኒቨርሲቲ ያለውን ተፅእኖ ተጠቅሞ የክርስትና ልጁ የህገ ቀኖና ወንበር እንዲይዝ
አደረገ፡፡ በግዜው ተቋሙ በከፍተኛ ደረጃ በጀስዊቶች ቁጥጥር ሰር ነበር፣ ይህም ወንበር ከድሮ ጀምሮ ከባድ ጀስዊት በሆኑ ሰዎች
ይያዝ የነበረ ነው፡፡ ውሻፕት ከግዜ ወደ ግዜ ይበልጥ እየተቀበለ የመጣው የዘመነ-አብርሆት ፍልስፍናዎች ከጀስዊቶች ጋር ያጋጩት
ነበር፡፡ እንዲህም ሁኖ ዉሻፕት ከጀስዊቶቹ የበላይነት ለማግኘት የሚደረግ አደረጃጀትና አፍራሽ ተግባራት ዘዴዎችን ይማር
ነበር፡፡ በዚህን ግዜ ነው ወደ ዉሻፕት ጭንቅላት ስለሚስጥር ማህበራት ሃሳብ ይገባ የጀመረው፡፡
“አስተዋይና ስልጣን ለመቆጣጠር በሴረኞች መንገድ በደንብ
የሰለጠነው ወጣቱ ውሻፕት ዓለምን ከሮማ ጀስዊቶች አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የሴረኞች ቡድን ሊያቋቁም ወሰነ፡፡” (Peter Tomkins, The Magic of Obelisks)
አንዳንዶች
እንደሚያምኑት ከሆነ በ1773 ላይ በጳጳስ ትእዛዝ የታገዱት ጀስዊቶች እራሳቸው አገዛዛቸውን ለመቀጠል ዉሻፕትን ተጠቀሙበት
የሚሉ ሲኖሩ ሌሎች ደሞ ባቫርያ ላይ የነበራቸውን እጅ ሊያላቅቅ ይታገል ነበር ይላሉ፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ ግን ዓለም ከሁሉም
ዓይነት መንግስታዊና ሃይማኖታዊ ተቋም ብትላቀቅ እንደምትጠቀም ያምናል፤ እኚህን ስርአቶች ዓለም አቀፋዊና ሚስጥራዊ በሆነ፣
ከሚስጥሩ በተቋደሱ ኮሚቴዎች መተካት ይመኝ ነበር፡፡ ይህን ግቡን ለማሳካትም የጀስዊቶችን ዘዴዎች ጀስዊቶችን ለመውጋት
ተጠቅሞበታል፡፡
ዉሻፕት
ምርምሩን እየቀጠለበት ሲሄድ የባእድ ሚስጥራት እውቀቱ እየጨመረ ሄደ፡፡ የዚህ ሚስጥራዊ እውቀት ሳቢነትን በሚገባ አጢኖት
ነበር፣ እኚህን ሃሳቦቹንም ለማሰራጨት የሞሶን ሎጆች (ቅርንጫፍ ቤቶች) ተስማሚ እንደሆኑ አወቀ፡፡ በዚህም መሰረት ፍሪሜሶን
ለመሆን ወሰነ፣ ይህ ሃሳብ ግን ሳቢነቱ ወድያው ቀረ፡፡
“ስለኢሉሲንያን ሚስጥራት ሳቢነትና የፓይታጎረሳውያን
ተከታዮች ሚስጥሮች ያሳደሩትን ተፅእኖ ሲያሰላ በጋለው ምናቡ መጀመርያ በግዜው የነበሩ የሜሶናዊ ተቋማት ተጠቅሞ ሃሳቦቹን
ማስፋፋት የውሻፕት አላማ ነበር፡፡ ከዚህ ከመጀመርያው እቅዱ ሊጨናገፍ ችሏል ምክንያቱም ባንድ በኩል ወደ ሜሶኖች ሎጅ
ለመቀላቀል ያለው ኪሳራ፣ በሌላ በኩል ያነበባቸው የሜሶኖች መጽሃፍት ብስለት የሌላቸውና በቀላሉ በብዙሃኑ ሊደረስባቸው የሚችሉ
በመሆናቸው ነበር፡፡” (Vernon L. Stauffer, The European Illuminati)
ከዚህ
ቀጥሎ ዉሻፕት የራሱ የሚስጥር ማህበር ማቋቋም እንዳለበት ይገባዋል፡፡ ሃሳቡን ለማስፋፋት ሊጠቅሙት የሚችሉ ሃያላን ሰዎችን
የያዘ፡፡
“በዚህም ምክንያት የግድ የራሱ ነፃ መስመር ማስጀመር
እንዳለበት አመነ፡፡ “የጥበባት ትምህርት ቤት” የያዘ፣ ከዓለሙ እይታ እራስን በመለየትና በሚስጥራት እውቀት ግምብ በመከለል፣
በቀሳውስቱ ስህተትና ራስወዳድነት ሳቢያ ለህዝብ እንዳይደርሱ የታገዱ ትምህርቶች ገና ላሉ (ለሚያምኑ) ወጣቶች በሙሉ ነፃነት
እነዚህ እውነቶች የሚሰጡበት ሞዴል የሚስጥር ማህበር መመስረት ጀመረ፡፡” (Vernon L. Stauffer, The European Illuminati)
የዉሻፕት
ድርጅት ግብ ቀላል ሆኖም ግዙፍ ነበር፡ ሁሉንም ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት መገልበጥና ከኢሉሚናቲ ሚስጥር በተቋደሱ
መተካት፡፡ እሱ እንደሚለው ሁለ ገብ ደስታ የሚመጣው መዓረግ፣ የበላይና የበታች እና ሃብት ሲወገዱ ነው፡፡ ከገፀ ምድር መሳፍንትና
ሃገራት ያለ አመፅ ይጠፋሉ፤ የሰው ዘር በሙሉ አንድ ቤተሰብ ይሆናል፤ ዓለምም በአመክንዮ የሚያምኑ መኖርያ ትሆናለች ይላል፡፡
ግንቦት 1፣ 1776 የባቫርያ ኢሉሚናቲ ተመሰረተ፡፡
የባቫርያው ኢሉሚናቲ
የውሻፕት
ኢሉሚናቲ ከትንሹ በአምስት ሰው ነበር የጀመረው፣ ከትንሽ ዓመታት በኋላ ግን ከሃያላን ሰዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ማህበሩ በዓለም ደረጃ ቀንደኛ
ፖለቲካዊ ሃይል ሆነ፡፡ ቀንደኛ ውሳኔ ሰጪዎች፣ ሃብታም ኢንዳስትሪያሊስቶች፣ ሃያላን መኳንንት፣ በባእድ አምልኳቸው ዝነኛ የሆኑ
ድብቅ ሰዎች ወዘተ. ማህበሩን ተቀላቅለው በሴራዊ ስራው መሳተፍ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶች የማህበሩ ፈጣን ስኬት ሊያገኝ የቻለው
ዉሻፕት አንድ ካግሊዮስትሮ ከሚባል ሰው ጋር መገናኘቱ ነው ይላሉ፡፡ ካግሊዮስትሮ በወቅቱ የነበረ ቀንደኛው የባእድ ሚስጥራት
አዋቂ ነበር፡፡ ሲመሰረት የባቫርያ ኢሉሚናቲ ሶስት መዓርጎች ነበሩት፡- ጀማሪ (ኖቪስ)፣ ሚነርቫል፣ ኢሉሚኔትድ ሚነርቫል
የሚሏቸው፡፡ እያንዳንዱ መዓርግ በፒራሚድ ቅርፅ ለተዋቀረው ማህበር ከላይ ያሉ አባሎች ሙሉ ቁጥጥር እንዲኖራቸው የየራሱ ግብ
የያዘ ነበር፡፡ እያንዳንዱን መዓርግ ባጭሩ እናየዋለን፡፡
ኖቪስ
ወደ
ባቫርያ ኢሉሚናቲ የሚገቡ አባሎች እንዲሳቡ የሚደረጉት የሚያምሩ ቃላት (ጥበብ እና መሻሻል አለን ለማለት) እና የባእድ
ሚስጥራት ሳቢነትን በመጠቀም ነበር የሚያማልሏቸው፡፡ ሲገቡ ግን ከነሱ በላይ የሆነ እጅግ በቁጥጥር ስር ያለና ከስሩ ያሉትን
ተቆጣጣሪ የሆነ የበላይነት ተዋረድ መኖሩን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ስለ ማህበሩ ፖለቲካዊ ግብ የሚነገራቸው ነገር አይኖርም፡፡
“አንዴ ከገባ በኋላ ኖቪሱ መመርያ/ ትምህርት የሚቀበለው
ባስገባው ሰው እጅ ነው የሚሆነው፣ ይህም በበኩሉ ከተማሪው የሱ የበላዮች ማንነትን በጥንቃቄ ይሸሽጋል፡፡ እንዲህ እንዲያነባቸው
የተፈቀደለት የማህበሩ ህጎች ከኖቪሱ የሚጠበቀው ሞራሉን ማስተካከል፣ የሰብአዊነት መርሆቹንና ማህበራዊነቱን ማስፋት፣ በተጨማሪም
የክፉ ሰዎች ሃሳቦችን መከላከል፣ ለተጨቆኑት መቆም፣ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ደሞ በዓለም ላይ የሚገባቸውን ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ
ነው ከኔ የሚጠበቀው ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል፡፡ ማህበሩን በተመለከተ ሊጣስ የማይችል ሚስጥራዊነት መጠበቅ እንዳለበት
አእምሮው ላይ በሚገባ ከተቀረፀበት በኋላ ከራስ ወዳድነት የሚመነጩ አመለካከቶቹና ምኞቶቹን መግራትና የሚገባውን ክብርና ሙሉ
ታዛዥነት በማህበሩ ላሉ በላዮቹ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ከኖቪሱ ቀንደኛ ተግባራት መካከል ለማህበሩ ማህደር የሚሆን ዝርዝር
ሪፖርት መፃፍን ያካትታል፡፡ ይህም ስለ ቤተሰቡ፣ ስለስራ ሂወቱ ያሉትን መፃህፍት ርእስ ሳይቀር፣ የግል ጠላቶቹ ስም ዝርዝርና
የተጣሉበት ምክንያት፣ ከባህሪው ጠንካራና ደካማ ጎኑ፣ የወላጆቹ የነበራቸው ወይም የሚታይባቸው የጎላ ስሜታቸው ምን እንደሆነ፣
የወላጆቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች ስም ዝርዝርወዘተ. በዝርዝር እንዲፅፍ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም ምልምሉ ከማህበሩ ያገኛቸውን
ጥቅሞችና ለማህበሩ ያደረጋቸውን አስተዋፅኦዎችን በተመለከተ ወርሃዊ ሪፖርት እንዲሰጥ ይጠበቅበታል፡፡ ማህበሩን ለማጠናከር ኖቪሱ
አዳዲስ ምልምሎችን በማስገባት የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል፣ ወደ ላይ መዓርጎች ለሚያገኘው እድገት እንዲህ አይነት አስተዋፅኦዎች
ላይ የሚመሰረቱ ናቸው፡፡ ላስገባቸው ሰዎች በተራው እሱ የበላይ ይሆንላቸዋል፣ እንዲህ ኖቪስ ሁኖ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ
ሲሆነው ወደ ቀጣይ መዓረግ ለሚደረግ ሽግግር መንገዱ ክፍት ይሆንለታል፡፡ (Vernon L. Stauffer, The European Illuminati)
ኖቪሱ
የበላዮቹ እድገት የሚገባው ነው ብለው ሲያምኑበት ወደ ሚነርቫል ያድጋል፡፡
ሚነርቫል
ሚነርቫል
የሚለው ቃል የሮማ የግጥም፣ የጥበብ፣ የንግድ፣ የሽመና፣ የእጅ ስራ፣ የአስማት እና የዘፈን አምላክ ከነበረችው ሚነርቫ
የተወሰደ ነው፡፡ ሁሌም ስትቀረፅ አብሯት ከሚሆን የጥበበኛነቷ ምልክት የሚሆን የጉጉት ወፍ ጋር ነው፡፡ ይቺ ጥንታዊ የሚስጥራት
ምልክት የሆነችው ሚነርቫ በኮንገረስ ላይብረሪ፣ በካሊፎርኒያ ግዛት ማህተም በመሳሰሉት ቦታዎች ላይ ትገኛለች፡፡
የባቫርያ ኢሉሚናቲ
የሚነርቫል አርማ ጉጉት ወፍ ነበረች፡፡ ከጎን የሚታዩት ሚነርቫል ላይ የደረሱ ባንገታቸው የሚያደርጉት ነው፡፡ ይቺ የጥበብ
ጉጉት የሚሏት እስከዛሬ ድረስ በከፍተኛ ቦታዎች እንደ ዋይት ሃውስ ቅጥር ግቢ አጠቃላይ ንድፉ፣ በአንድ ዶላር የገንዘብ ኖታ
ላይ፣ የቦኸምያን ክለብ የሚባለው አፀያፊ ማህበር ምልክት ወዘተ. ተቀርፃ
ትገኛለች፡፡
ከላይ ካፒቶል ሂል
(የዋይት ሃውስ ቅጥር ግቢ የተሰራበት ንድፍ በጉጉት ወፍ ሲሆን በቀኝ በኩል ደሞ የቦኸምያን ግሮቭ አባሎች አርባ ጫማ ቁመት
ካለው ግዙፍ የጉጉት ወፍ ሃውልት ስር ችቦ ይዘር በምሽት ባእድ አምልኮ ሲያካሂዱ በሴራ ታሪክ ተመራማሪው አሌክስ ጆንስ
ያነሳቸው ምስል ይታያል፡፡
ከጎን የጉጉት ወፍ የአሜሪካ ዶላር ላይ፡፡
ይህ
ሁለተኛ የነበረው የኢሉሚናቲ መዓርግ የማሳመን/ስብከት ስራ የሚሰራበት ነው፡፡ ምልምሎቹ ስለማህበሩ መንፈሳዊ ዓላማ ትምህርት
የሚያገኙበት ሲሆን ስለ ዉሻፕትና የቅርብ አጋሮቹ እውነተኛ ዓላማ ግን የሚሰሙት ነገር አይኖርም፡፡
“ኖቪሱ ወደ ሚነርቫል መዓርግ በሚያደርገው ሽግግር ወቅት
የሚኖረው ስነ ስረዓት በኖቪሱ አእምሮ የማህበሩን ግብ በተመለከተ ሃብታሞችንና ሃያሎችን ማንበርከክ እንደሆነ ወይም የስጋዊ
(የሲቪል) እና ሰማያዊ መንግስታትን መገልበጥ እንደሆነ በሚመለከት በጭንቅላቱ ሊቀር የሚችልን ጥቂትም ብትሆን ጥርጣሬን ማጥራት
ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተጨማሪም እጩው ለሰው ልጆች ጥቅም የሚሰራ፣ ዘላለማዊ ሚስጥር ያዥነቱን፣ የማይገረሰስ ታማኝነቱን፣ እና
ለማህበሩ የበላዮችና መመርያ ደንቦች ከማያጠራጥር ከበሬታ ጋር ታዛዥ እንደሚሆን እና ማናቸውንም የግል ፍላጎቶቹን ለማህበሩ ሲል
መስዋእት የሚያደርግ መሆኑን ቃለ መሃላ ይፈፅማል፡፡” (Vernon
L. Stauffer, The European Illuminati)
ሚነርቫሎች
አንዳንድ የበላዮቻቸውን (ኢሉሚኔትድ ሚነርቫሎችን) እንዲገናኙና እንዲወያዩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ እንዲ አይነቱን ማበረታቻ ማግኘት
መዓርጉን ለሚቀላቀሉ አዲሶች ከፍተኛ ተነሳሽነትን ይፈጥርላቸው ነበር፡፡
ኢሉሚኔትድ ሚነርቫል
ከሚነርቫሎቹ
የሚመረጡትና በሶስተኛ መዓርግ የሚቀመጡት ኢሉሚኔትድ ሚነርቫሎች በተግባራዊው ዓለም አንዳንድ ስራዎችን እንዲሰሩ በግልፅ
የሚቀመጡ ሃላፊነቶች ይሰጧቸዋል፡፡ አብዛኛው ስራቸው የሚያካትተው የሰው ልጅንና ለመምራት የሚደረጉት ዘዴዎችን ፍፁም ማድረግን
እንዲያጠኑ ይደረጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ኢሉሚኔትድ ሚነርቫል በስሩ ሚነርቫሎች የሚሰጡት ሲሆን እነዚህን በሚገባ መርምሮ በሚገባቸው
አቅጣጫ ያሰማራቸዋል፡፡ እኚህ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አባሎች በሰፊው በብዙሃኑ ላይ ሊደረግ ስለሚችን ስራ መሞከርያ ያደርጓቸዋል
ማለት ነው፡፡
“የበላዮቻቸው ይገባቸዋል ብለው የሚያስቧቸው ከሚነርቫል
ወደ ኢሉሚኔትድ ሚነርቭል ያሸጋግሯቸዋል፡፡ በዚህም ግዜ የሚኖረው ሰፊ የሽግግር ስነስረአት በምልምሉ ጭንቅላት ውስጥ በማህበሩ
ወደ ላይ ለሚያደርገው ጉዙ ሂወቱን ይበልጥ እያጠራ መሄድ እንደሚጠበቅበት እና በዚህኛው አዲስ መዓርግ ውስጥ ባለበት ወቅት
ሰዎችን እንዴት መምራት ይቻላል የሚለውን ጥበብ መካን ዋና ግቡ እንደሆነ ይቀበላል፡፡ ይህን ለማሳካት ማለትም ጥሩ የስነ ልቦና
ባለሙያ እና የሰዎች ንቃተ ህሊና መሪ ለመሆን ያለማቋረጥ በስሩ የተደረጉት እንዲማሩ የመጡትን የሚነርቫሎቹን ተግባራት፣ ዓላማ፣
ምኞት፣ ስህተቶችና በጎ ጎናቸውን ያጠናል፡፡ ለዚህ ከባድ ሃላፊነት የሚሆን ውስብስብ የመመርያ ጥራዝ ይሰጠዋል፡፡
“ሚነርቫሎቹ በሚያደርጉት ስብሰባዎች በቋሚነት ከመገኘት
በተጨማሪም፣ እራሳቸው ኢሉሚኔትድ ሚነርቫሎችም በወር አንዴ ይሰባሰባሉ፡፡ በዚህም ስለ ተማሪዎቻቸው ያለ መረጃና ለወደፊቱ
የተሸለ ውጤት የሚያገኙበትን መንገድ ይወያዩበታል፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች የሚነርቫሎቹ መዝገቦች ታይተውና ታርመው ለማህበሩ
የበላዮች ይተላለፋሉ፡፡ (Vernon L. Stauffer, The European Illuminati)
ከዚህ
መሰረታዊ አደረጃጀት ቅርፅ በመነሳት ኢሉሚናቲ መስፋፋት ጀመረ፡፡
ዉሻፕት ዋና ግቡን፡- ፍሪሜሶኖችን ሰርጎ መግባት ያሳካ ዘንድ አሁን ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡
ፍሪሜሶኖችን ሰርጎ መግባት
ኢሉሚኒናቲ
በተመሰረተ በአመቱ በ1777 ዉሻፕት ሙኒክ ሚገኘውን የበጎው ምክር ቴዎድሮስ
(Theodore of Good Counsel) የተሰኘ ሎጅን
ተቀላቀለ፡፡ ወደዚህ ሎጅ አመለካከቶቹን አስገብቶ ማስረፅ ብቻ ሳይሆን ሎጁን ባጠቃላይ ወደ ኢሉሚናቲ ማህበር ስር እንዲሆን
አድርጓል፡፡ (Manly
P. Hall, Masonic Orders of Fraternity)
በኢሉሚናቲና በፍሪሜሶን መሃከል ያለው ትስስር ግን እርግጥ
የሆነው በ1780 ባሮን አዶልፍ ፍራንዝ ፍሬደሪክ ኒጅ (Baron
Adolf Franz Friederich Knigge) የተባለ በዚህ ዙርያ
ተሰሚነት የነበረው ሰው የዉሻፕት ማህበርን ሲቀላቀል ነበር፡፡ ይህ የጀርመን ዲፕሎማት የሆነው ሰው የነበረው የሜሶናዊ ትስስር
እና የማደራጀት ችሎታው በኢሉሚናቲ በሚገባ ነበር ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡ ኒጅ ለኢሉሚናቲ ሁለት ወሳኝ ነገሮችን አከናውኗል፡
የማህበሩን የመዓረግ ተዋረድን በማስተካከል አዳዲስ ከፍተኛ መዓርጎችን ፈጥሯል በተጨማሪም የሜሶን ሎጆች በዚህ ስርአት ሙሉ
ለሙሉ እንዲወሃዱ አስችሏል፡፡ በዚህም በኢሉሚናቲ ፍሪሜሶን መሃከል ትስስር ፈጥሯል፡፡
ከጎን፡ ኒጅ፣ ተፅእኖ
ፈጣሪ የሆነው የጀርመን ዲፕሎማቱና ባእድ አምልኮ ተከታዩ በ1780 ኢሉሚናቲን ተቀላቀለ፡፡ እዚህ በምስሉ ላይ የተደበቀው እጅ
ምልክት እያሳየ የተሳለው ስእል ይታያል፡፡
ከጎን፡
ለኢሉሚናቲ የሰራው አዲሱ ስርአት ፍሪሜሶኖችንና ሌሎች ሃያላን ግለሰቦችን ለመሳብ አስችሏል፣ ይህ ወድያውኑ ለማህበሩ ፈጣን
እድገት ረድቶታል፡፡
ኒጅ
የማህበሩ የመጀመርያዎቹን መዓርጎች እንዳሉ አልነካቸውም፡፡ ከነዚህ በኋላ የሜሶን መዓርጎችን ጨመረ፣ በዚህም የፍሪሜሶን
ወንድማማችነትን የኢሉሚናቲ ክፍል ወይም ትንሽ አካል አደረገው፡፡ ኒጅ ለአዲስ ምልምሎቹ ኢሉሚና ትክክለኛውና ያልተበረዘው
ጥንታዊውን ፍሪሜሶን ሚስጥር የያዘ መሆኑን ይናገር ነበር፡፡ የቀላቀላቸው የሜሶን መዓርጎችም ሜሶኖቹን በመሳብ ወደ ራሱ ከፍተኛ
ማርግ ለማሸጋገር ነው፡፡ (Manly P. Hall, Masonic Orders of Fraternity)
የማህበሩ
የላይኛው መዓርጎች ለተመረጡ ጥቂቶች ብቻ የተወሰኑ ሲሆኑ እነዚህም ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉና ሃያላን ግለሰቦችን ብቻ የሚያካትት
ነበር፡፡ ከፒራሚዱ ጫፍ ላይ ያሉት የማህበሩ የበላይ ገዢዎች ማንነት አይታወቅም እስከ ዛሬ ድረስም በርግጠኝነት ለመናገር
ያስቸግራል፡፡ የኒጅ ስልት ለኢሉሚናቲ ከፍተኛ ስኬትን በማስገኘት ሃይለኛ ሃይል እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በዚህ አሰራር መሰረት
ከፍሪሜሶን ብዙዎቹን መሳብ ችሏል ታዋቂ መኳንንትን ጨምሮ ፈላስፎችንና ስነፅሁፍ ሰዎችን በስሩ ማድረግ ችሏል ከነዚህም ለምሳሌ፡
ፈላስፋው ኸርደር፣ ባለቅኔው ጎተ፣ የትምህርት ስርአት ፈላስፋው ፔስታሎዚ ይገኙበታል፡፡ በ1784 ከሁለት ሺህ እስከ ሶስት ሺህ
አባሎች እንዳሏቸው አመራሮች ይጎረሩ ነበር፡፡ (Manly P. Hall, Masonic
Orders of Fraternity)
ይህን
ስኬቱን ግን ዉሻፕት ለረዥም ግዜ ሊያጣጥም አልቻለም፡፡ በመንግስታትና ሃይማኖቶች ላይ የሚሰራው ሴራ በመላ አውሮፓ በጥርጣሬ
እንዲታይ አደረገው፡፡ በዚህም መሰረት የባቫርያ ገዢ ማናቸውም ማህበራትና ወንድማማችነቶች ያለ ህጋዊ ፈቃድ መንቀሳቀስ
እንደማይችሉ አዋጅ አስተላለፈ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውሻፕት እና በማህበሩ የበላይ መሪዎች መሃከል መለያየት መፈጠር ጀመረ፡፡
በዚህ መሃል አንዳንድ የማህበሩ አባሎች ወደመንግስት በመሄድ ምህበሩ ላይ መመስከር ጀመሩ፡፡
“የማህበሩ ጠላቶች ሲያስወሩበት የነበረው በማህበሩ ወዳጆች
አፍ መረጋገጥ ጀመረ፡፡ መሪዎቹ በሰጡት ቃል መሰረት የኢሉሚናቲ ስርአት ሃይማኖትንና መንግስትን ለመገልበጥ የተደራጀ መሆኑ
ታየ፣ የመርዝ ቀማሚዎችና የሃሰት ሰነድ ሰሪዎች ቡድን፣ የወረደ ሞራልና አስቀያሚ ስብእና ያላቸው ሰዎች ስብስብ መሆኑ
ተጋለጠ፡፡” (Manly
P. Hall, Masonic Orders of Fraternity)
በ1788
በመንግስት በተወሰደበት እርምጃ ኢሉሚናቲ ተበተነ፡፡ ይህ ግን አንዳንዶች እንደሚሉት የማህበሩ መጨረሻ አይደለም፡፡ ኢሉሚናቲ
ከባቫርያ የሜሶን ሎጆች ውጪም በሌሎች ሃገሮች ገብቶ እንደነበር መረሳት የለበትም፡፡ በሌላ አነጋገር ኢሉሚናቲ አልተደመሰሰም
ነበር፣ ይበልጥ በድብቅ ወደመንቀሳቀስ ገባ እንጂ፡፡ ከአመት በኋላ የሆነው ክስተት ኢሉሚናቲ ከምንንም ግዜ በላይ በንቃት
እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ያሳየ ነበር፡- የፈረንሳይ አብዮት፡፡
የፈረንሳይ አብዮት
በ1789
የደረሰው የፈረንሳይ ዘውድ በሃይል መገልበጥ ለብዙዎች የሚያመላክተው ከባህላዊ ተቋማቱ ይልቅ የአብዮተኞቹ ጃኮቢኒዝምና
ኢሉሚኒዝም የበላይነት ማግኘትን ነው፡፡ በወቅቱም የታወጀው የሰብአዊ መብቶች እወጃ ሰነዱ ሜሶናዊና ኢሉሚናቲ ሃሳቦችን ወደ
ፈረንሳይ መንግስት ስርአት ያስገባ ነበር፡፡ የሃገሪቱ አዲሱ መፈክሯ የሆነው፡ ነፃነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት አስቀድሞ
ለዘመናት በፈረንሳይ ፍሪሜሶን ሊጆች ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ነው፡፡
የአብቱ
መታሰብያ በሚለው ፅሁፍ ላይ እንዳየነው ዋናው የዶክመንቱ ቅጂ ብዙ የሚስጥር ማህበሩን ምልክቶች የያዘ እንደሆነ አይተናል፡፡
መጀመርያ ከላይ ሶስት መአዝን ውስጥ ያለው የሚያበራው የሆሩስ ዓይንን እናያለን፡፡
ከአርእስቱ ስር እራሱን የሚበላው የሂወት ኡደትን
ያለማክታል የሚሉት የኦሮቦሩስ እባብ ምስል ይገኛል፡፡ ይህ ከአልኬሚ፣ ግኖስቲሳውያን እና ኸርመቲዝም ሁሉም ከሜሶን ትምህርቶች
ኮር የሆኑት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከኦሮቦሮሱ ስር ቀዩ የፍሪግያ ኮፍያ ጦር ላይ ተሰክቶ ይታያል፡፡ ይህ በወቅቱ በአለም ዙርያ
የአብዮቶች ምልክት የነበረ ነው፡፡ የአዋጁ ክፈፍ የታጠረው በሜሶናዊ ጥንዶቹ ቋሚ አምዶች ነው፡፡ እነዚህ ሁለት አምዶች የሜሶን
ቀንደኛ ምልክት ናቸው፡፡ ሌሎችም አሉበት፡፡
ኢሉሚናቲ ላይ የደረሰ ተቃውሞ
የባቫርያ ኢሉሚናቲ ጠፍቷል ቢባልም ሲያሰራጫቸው የነበሩ
ሃሳቦች ግን እውን ሁነዋል፡፡ ዋና ግቦቹ ባጭሩ፡- (1) መንግስታትን ማስወገድ፤ (2) የግል ንብረት ባለቤትነትን
ማስወገድ፤ (3) የውርስ መብትን ማስወገድ፤ (4) ሃገራዊነትን ማስወገድ፤
(5) ሁሉንም ሃይማኖቶችን ማስወገድ፤ (6) ቤተሰባዊ ስርአትን፣
ግብረገባዊ እሴቶችን እና የህፃናት ትምህርት ቁጥጥርን ማስወገድ፤ (7) የዓለም መንግስት መመስረት
ናቸው፡፡ እኚህ አላማዎች በ19ኛው እና በ20ኛው ክ/ዘመን ለተስፋፉት ፖለቲካዊ እና የተለያዩ
ፍልስፍናዊ ዶግማዎች መሰረት የሆኑ ናቸው፡፡ በወቅቱ ፍሪሜሶኖችና ሮዚክሩሽያኖች በስፋት ሲንቀሳቀሱ ነበሩ፣ ኢሉሚናቲም በነዚህ ውስጥ
ተሸሽጎ ህልውናውን ሲያስቀጥል ነበር፡፡ አውሮፓ አዳዲስ መደቦች ስልጣን የሚቆጣጠሩበት የከፍተኛ ግርግር ግዜ ነበር ስታሳልፍ የነበረችው፡፡
በወቅቱም ብዙሃኑ እያዩ ያሉትን ለውጦች ቅርፅ የሚያሲዙት ሃይሎች እነማን እንደሆኑ የሚያስረዱ ምሁራን መታየት ጀመሩ፡፡
ሊዮፖልድ ሆፍማን የተሰኘ ፍሪሜሶን ኢሉሚናቲዎች ወንድማማችነቱን
መርዘውታል በሚል እምነት ተነሳስቶ
Wiener
Zeitschrift በሚል ህትመቱ በተከታታይ ፅሁፎችን ያወጣ ነበር፡፡
እንደሚያስረዳው ከሆነ የታችኞቹ የኢሉሚናቲ መዓርጎች የተሰረዙ ሲሆን ከላይ ያሉት መዓርጎች ግን አሁንም እንዳሉ ያስረዳል፡፡
ፍሪሜሶንም በኢሉሚናቲ ቁጥጥር ስር እንዲገባ እየተደረገ እንደሆነና የነሱን ግብ ለማሳካት መሳርያ እየተደረገ እንዳለም
ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም የፈረንሳይ አብዮት የአመታት የኢሉሚናቲ ፕሮፖጋንዳ ውጤት እንደሆነ ይናገራል፡፡
በ1797 ጆን ሮቢንሰን የተባለ የስኮትላንድ ምሁርና
የፈጠራ ሰው (ሳይረንን የፈጠረ) “Proofs of a Conspiracy against All the Religions and
Governments of Europe, carried on in the Secret Meetings of the Free Masons,
Illuminati, and Reading Societies”
በተሰኘ መፅሃፉ ሴራውን የሚጋልጥ ማስረጃ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ ለፍሪሜሶን ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ሰው ወንድማማችነቱ
በኢሉሚናቲዎች እንደተጠለፈ ሲገባው ከእንቅልፉ ነቅቷል፡፡
ኦግስቲን ባሩኤል የተባለ የፈረንሳይ ጀስዊት ቄስም
በ1797 የፈረንሳይ አብዮትና የባቫርያ ኢሉሚናቲን ትስስር የሚያሳይ መፅሃፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡ Memoirs Illustrating the History of Jacobinism በተሰኘ የአራት ቅፅ መፅሀፉ
“ነፃነትና እኩልነት” የሚለው መፈክር ወደቀደሙት የመቅደሱ ባለሟሎች (ቴምፕላርስ) የተገኘ ሲሆን ይህ ጭብጥም በማህበሩ ከፍተኛ
መአርግ ላይ ሲብራራ በነገስታትና ዘውዶቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ውጊያ እንዲታወጅ የሚያደርገው በተጨማሪም በክርስቶስና መቅደሱ ላይም
ነው፡፡ በተጨማሪም ኢሉሚናቲ እንዴት ፍሪሜሶንን መቆጣጣር እንደቻለ ዝርዝር ሁኔታውን ያሳያል፡፡
“ባሩኤል እንደሚለው ከሆነ
ከታች ያሉት ሜሶኖች ብቻ ሳይሆን በዉሻፕት የተታለሉት፣ የዉሻፕት የራሱ ኢሉሚናቲዎችም ኢዮፓገስ የሚባል ሌላ ከፍ ያለ የሚስጥር
የበላይ መሪዎች አካል አለ ማህበሩን በሙሉ የሚቆጣጠሩና ሚስጥራዊ ግቡን የሚያውቁ አሉ በማለት አታሏቸዋል፡፡ ለባሩኤል እንደ ላሮቼፎካልድ፣
ላፋዬቴ፣ እና የኦርሊንሱ መስፍን የመሳሰሉት የአብዮቱ ቀንደኛ መሪዎች የኢሉሚናቲ ኤጀንቶችና ይበልጥ ፅንፈኛ የሆኑት እንደነ ዳንቶን
ያሉት አነሳሾች መሳርያ የሆኑ ናቸው፡፡ ባሩኤል በተጨማሪም የፈረንሳይ ሜሶን ባጠቃላይ ወደዉሻፕት አብዮታዊ አላማ አገልጋይነት መቀየሩን
ይናገራል፣ ሎጆቹም የደም መፋሰስ እቅድ አውጪዎች የሚስጥር ኮሚቴ መቀመጫ ሁነዋል ይላል፡፡ (Peter Tomkins, The
Magic of Obelisks)
ወደ አሜሪካ መስፋፋት
የአሜሪካ
መስራች አባቶች የሚባሉት አብዛኞቹ የሚስጥር ማህበራት አባሎች ነበሩ፣ ፍሪሜሶንም ሆነ ሮዚክሩሽያኖች ወይም ሌላ፡፡ አንዳንዶቹ ወደ
አውሮፓ ጉዞ አድርገው የነበሩ ሲሆን የኢሉሚናቲ ዶክትሪንን ለማወቅ የቻሉ ነበሩ፡፡
የባቫርያ
ኢሉሚናቲ በግልፅ ይንቀሳቀስበት በነበረ ወቅት ከ1776 እስከ 1785 ቤንጃሚን ፍራክሊን በፈረንሳይ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር
ሁኖ ያገለግል ነበር፡፡ በቆይታው ወቅትም Les Neufs Soeurs የተባለ ሎጅ ግራንድ ማስተር
ወይም ዋና አለቃ ለመሆን ችሎ ነበር፣ ይህ ሎጅ የኢሉሚናቲ ተፅእኖ ያለበት የፈረንሳይ ግራንድ ኦርየት ሎጅ አካል ነበር፡፡ ይህ
ሜሶናዊ ድርጅት የባቫርያ ኢሉሚናቲ የፈረንሳይ አካላቸው ነበር፡፡ በአሜሪካው የነፃነት አብዮት ወቅት የፈረንሳይ ድጋፍ እንዲያገኝ
ሰፊ ሚና የተጫወተ ሲሆን በኋላ ላይም በፈረንሳይ አብዮት እንዲነሳ ሰፊ ድርሻ ነበረው፡፡
በ1799
የጀርመን ሚኒስትሩ ጂ.ደብሊው. ስናይደር የኢሉሚናቲ እቅድን በተመለከተ ጆርጅ ዋሽንግተን እንዲጠነቀቅ ሲነግረው፣ “ሁሉን የኢሉሚናቲ
አስቀያሚና አደገኛ እቅዳቸውንና ዶክትሪናቸውን” እንደሚያውቀው ነግሮታል፡፡ በደብዳቤውም እንደሚከተለው ብሎ ደምድሞ ነበር፡ “በዚህ
ሃገር ያሉት ሎጆች የትኞቹም ቢሆኑ የኢሉሚናቲ ናቸው በሚባሉት መርሆች አልተበከሉም፡፡” ብሏል፡፡
ከወር
በኋላ ለስናይደር በፃፈው ሌላ ደብዳቤ በጉዳዩ ላይ እንዲህ ሲል ዋሽንግተን አክሎበታል፡
“ማለት የፈለኩት የኢሉሚናቲ ዶክትሪኖችና የጃኮቢኒዝም መርሆች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ
አልተስፋፉም ለማለት አይደለም፡፡ በተቃራኒው ይህ ሃቅ ስለመኖሩ በውበቱ ከኔ በላይ ማንም የሚያምን የለም፡፡
“ለማለት የፈለኩት በዚህ ሃገር ያሉት የፍሪሜሶን ሎጆች እንደ ማህበር ይህን ሴጣናዊ መርሆች …
ለማስፋፋት የሚሰራ የለም ለማለት ነው፡፡… ግለሰቦች ሊያደርጉት ይችላሉ፣ መስራቹ ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ዲሞክራሲያዊ
ማህበረሰቦች ለመመስረት የተጠቀሙበት መሳርያ፣ እነዚህ ዓላማዎችን ይዘው የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ከራእያቸው ህዝብን ከመንግስታው
የመለያየት የነበራቸው ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን ከጥያቄ ውስጥ ለማስገባት በማይቻል መልኩ ማስረጃው አለ፡፡”
ኢሉሚናቲን
በተመለከተ ጆርጅ ዋሽንግተን የፃፈው ደብዳቤ ዋና ቅጅ አካል፡፡
ከዚህ ደብዳቤ በመነሳት ጆርጅ ዋሽንግተን ስለ ኢሉሚናቲ
ዶክትሪኖች አሳምሮ ያውቅ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ የሜሶናዊ ተቋማት በአሜሪካ እንዲህ ያደርጋሉ ብሎ ባያምንም ግለሰቦች ግን
ሊሞክት እንደሚችሉ ይቀበላል፡፡
ከባቫርያ ኢሉሚናቲ በኋላ
ዛሬ ኢሉሚናቲ የሚለው ቃል አንድ የአለም መንግስት፣ አንድ መገበያያ ገንዘብና አንድ ሃይማኖት ያለው ለመመስረት የሚሰሩ
ቡድኖች መግለጫ ተደርጎ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህ ቡድን ከዋናው ከባቫርያ ኢሉሚናቲ የተገኘ መሆኑን ለመወሰን የሚከብድ ቢሆንም
መርሆቹና ዘዴዎቹ ግን የዋናው ቅጥያ ናቸው፡፡ ባእድ ተከታይ
ቁንጮዎችን ለመግለፅ የምንጠቀምበት ስም ሊለያይ ይችላል፡፡ ስሙን ማግኘት ላይ አይደለም ዋናው ነጥቡ ያለው፣ መታወቅ ያለበት
ለዘመናት የኖረው ምንነቱ ነው፡፡
ማንሊ ፒ. ሃል
እንደሚለው የባቫርያ ኢሉሚናቲ ለዘመናት የኖረ የሚስጥር ወንድማማችነት አካል ነው፡፡ እንደሃል አባባል ይህ ወንድማማችነት
እንዳንዴ በተለያዩ ስሞችና ምልክቶች እራሱን ይገልጣል፡፡ ይህ ማለት ናይትስ ቴምፕላር፣ ፍሪሜሶን፣ ሮዚክሩሽያን እና ኢሉሚናቲ
ሁሉ ተደብቆ ያለ ሃይል ግዝያዊ መገለጫ ናቸው ማለት ነው፡፡
ኢሉሚናቲ ዛሬ
ዛሬም የኢሉሚናቲ
አጀንዳች እየተተገበሩ ከሆነ ምን አይነት ቅርፅ ነው የሚይዙት? ከጥንታዊ ባእድ ሚስጥራትና መንፈሳዊ መአዝን ያየነው እንደሆን
አንዳንድ ዘመናዊ የሚስጥር ማህበራት ለምሳሌ እንደ ኦ.ቲ.ኦ. (Ordo
Templi Orientis) ያሉት የኢሉሚናቲ
ወራሾች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ተመራማሪዎች ደሞ ከሚታወቁት የዛሬዎቹ 33 የፍሪሜሶን መአርጎች ውጪ ተጨማሪ የኢሉሚናቲ
መአርጎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ እንደ ስማቸው ሚስጥራዊ ስለሆኑ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ከባድ ነው፡፡
በፖለቲካዊው
በኩል ዘመናዊ የኢሉሚናቲ እንቅስቃሴ በቀለለ መልኩ መታየት ይቻላል፡፡ ጥብቅነቱ እየጨመረ የሄደና ይበልጥ በጥቂቶች እጅ እየገባ
ያለ ቡድን የወሳኝ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ሃላፊነትን እየተረከበ ይገኛል፡፡ ዛሬ ዓለማቀፋዊ ኮሚቴዎችና ድርጅቶች፣ በህዝብ
ከተመረጡ ባለስልጣናት በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን እየወሰኑ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ
አይነት ክስተት በዓለም ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ እየታየ ያለ ነው፣ ከመንግስታት ይልቅ ከዓለም ቁንጮዎች የጠውጣጡ በህዝብ
ያልተመረጡ ሽፍን-ገዢዎች ቀስ በቀስ የዓለም ሃይል ሚዛን ማእከል እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
“በሌላ ፖለቲካዊ መስክ እንደ የውጭ ግንኙነት መማክርት (Council on Foreign Relations) እና እንደ የዓለም ኢኮኖሚያዊ መድረክ (World
Economic Forum) ያሉት
ይገኛሉ፡፡ እዚህ በፖለቲካ፣ በቢዝነስ፣ በፋይናንስ፣ በትምህርት እና በሚድያ ላይ መሪዎችን እናገኛለን፡፡ አንድ የሚያረጋቸውም
ለሁሉም ችግር ሉላዊ መፍትሄ የሚናገሩ መሆናቸው፣ በከፍተኛ ሃላፊነትና ተፅእኖ አድራጊነት ላይ ያሉ መሆናቸው ሲሆን እነዚህ
ግሩፖች [ያልተመረጡት፣ ሽፍን-ገዢዎች] የመክብቡን የተለያየ ደረጃ ይወክላሉ [ሁሉም በእኩል ደረጃ ሚስጥራዊ ግቡን
አያውቁም፡፡] አብዛኞቹ አባሎች እንዲህ ከታዋቂ ሰዎች ጋር መሰብሰባቸው ብቻ ክብር ሁኖ የሚያስደስታቸው ናቸው፡፡ ሆኖም
እንደዚህ አይነት ቡድን ከላይ ስንደርስ የዓለም መንግስትን የሚደግፍ ነው-
ከላይ ማእከል ተደርጎ የተደራጁ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተቋማትን እንዲያንቀሳቅሱ ሃላፊነት በሚሰጣቸው ሙያተኞችና እቅድ
አውጪዎች ተዋቅሮ የሚተዳደር ነው፡፡ አባል [ሃገሮች] ድንበር ዘለል በሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ድምፃቸውን
እንዲያሰሙ ቢፈቀድላቸውም እንኳ የቡድኑ የውስጥ ኮር የረዥም ግዜ እቅድን ላይደግፉ (እንዲያውም ላያውቁ) ይችላሉ፡፡ እነዚህ
ቡድኖች ብዙውን ግዜ ስብሰባቸውን በሚስጥር የሚያከናውኑ ሲሆን የአባሎቻቸው ስም ዝርዝር ግን የህዝብ መዝገብ ናቸው፡፡
ማእከላዊው አጀንዳ ነው የሚሸሸገው፡፡ (James Wasserman, The
Mystery Traditions)
ከነዚህ የቁንጮዎች ቡድን ዋነኞቹ ዓለምአቀፍ የቀውስ ቡድን (International
Crisis Group)፣ የውጭ
ግንኙነት መማክርት (Council on Foreign Relations)፣ የዓለም ኢኮኖሚያዊ መድረክ (World Economic Forum)፣ የብሩኪንግስ ተቋም (Brookings
Institution)፣ ቻንታም ቤት (Chatham House)፣ የሶስትዮሹ ኮሚቴ (Trilateral
Commission) እና
የቢልደርበርግ ቡድን (Bilderberg Group) ይገኙበታል፡፡ የቦኸሚያን ክለብ የሚባለው ደሞ እንጋዳ
በአላትና ስነ ስረአቶች የሚከናወኑበት የዓለም ቁንጮ ሰዎች መሰባሰብያ ነው፡፡ ካሊፎርኒያ የሚገኘው የክለቡ አፀድ ቦኸሚያን አፀድ የሚባለው
መሰባሰብያቸው የሚገኘውን 40 ጫማ የሚያክለውን ግዙፍ የጉጉት ወፍ ሃውልት ምስል ከላይ አይተነዋል፣ በተጨማሪም ከባቫርያ ኢሉሚናቲ
ሚነርቫሎች ባንገታቸው ከሚያደርጉት ጋር የሚመሳሰል የጉጉት ወፍ ነው የክለቡ አርማ፡፡ (ምስል ከጎን)
የነዚህ ሁሉ
ብድኖችን አባሎች ከመረመርን ሃያላን ፖለቲከኞች፣ የድርጅቶች የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ ምሁራን፣ ብዙም የማይታወቁ ግለሰቦችንና
ዝነኛ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ እኚህ ሰዎች ከግላቸው የጀመሩ ሳይሆን በቤተሰባቸው የዘር ሃረግ አስቀድሞ ቁልፍ የኢኮኖሚና ፖለቲካ
ቦታዎችን መቆጣጠር የቻሉ ቤተሰቦች የሚገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የባንክ ስርአቱን፣ የነዳጅ ኢንዱስትሪውን፣ መገናኛ ብዙሃኑን
የተቆጣጠሩት ቤተሰቦች፡፡ የነዚህ ቤተሰብ ስሞችን የአለም ታሪክን እጣ ፈንታ በወሰኑ ቁልፍ ክስተቶች በስተጀርባ እናገኛቸዋለን፣
ለምሳሌ በአሜሪካ ገንዘብ በባንክ ከበርቴዎች ቁጥጥር ስር እንዲገባና አሜሪካን ከበርቴዎች በጭሰኝነት እንዲይዟት ያደረገው
የ1913 የማእከላዊ ባንክ ማለትም ፌደራል ሪዘርቭ ምስረታ ላይ ስማቸው ይገኛል፡፡ ይህን የሚያረጋግጥልን የ1982 የፍርድ ቤቱ
ውሳኔ ነው፡ “ሪዘርቭ ባንኮቹ የፌደራል [መንግስት] ለ FTCA [በጉዳት
ግዜ የካሳ ወይም ዋስትና የሚሆን] ተብሎ አይደለም የተቋቋሙት፣ በግል ይዞታና ቁጥጥር ያሉ ነፃ ኮርፖሬሽኖች ናቸው፡፡” ሲል የአሜሪካ ህዝብ ጭሰኝነቱን ተረድቷል፡፡ ይህ
ካፒታሊዝም አይደለም ይህ የመቧደን ሴራ ሲሆን በህገ መንግስታቸውም ወንጀል ነው፡፡ ደሞስ በምን ስሌት ነው ብሄራዊ መገበያያ
ገንዘብ በግለሰቦች እጅ እንዲሆን የሚፈቀደው፡፡ ይህ ስራ የሴራ ውጤትና የታገሉትንም ያጠፋ ነው፡፡
Bloodlines of the Illuminati በሚለው መፅሃፉ አነጋጋሪው የሴራ ታሪክ ፀሃፊው ፍሪትዝ
ስፕሪንግመየር የዛሬዎቹ ኢሉሚናቲዎች አስራሶስት ሃያል ቤተሰቦች የዘርግንድ የሚገኙ መሆናቸውን ያስረዳል፣ የነዚህ ቤተሰቦች
ቅድም አያቶች ከባቫርያው ኢሉሚናቲ ጋር የቀርብና ሩቅ ግንኙነት የነበራቸው ናቸው ይላል፡፡ ስፕሪንግመየር እንደሚለው ከሆነ 13
ቤተሰቦች የሚከተሉት ናቸው፡ አስቶር፣ በንዲ፣ ኮሊንስ፣ ዱፖንት፣ ፍሪማን፣ ኬነዲ፣ ሊ፣ ኦናሲስ፣ ረይኖልድ፣ ሮክፌለር፣
ሮዝስቻይልድ፣ ራሴል እና ቫን ዱይን ናቸው፡፡ (Fritz Springmeier, The Bloodlines of the Illuminati)
እነዚህ ቤተሰቦች
ዛሬ በሚቆጣጠሩት ፖለቲካዊና ቁሳዊ ሃይል በዓለም ላይ የበላይነት እንዳላቸው ጥያቄ የለውም፡፡ ኢሉሚናቲ የምንለውን ቡድን ኮር
ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ጥያቄው የሚሆነው አዲስ የዓለም ስርአት ለመፍጠር እያሴሩ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከሮክፌለር የሂወት
ጻሪክ መፅሀፉ የተወሰደውን ጥቅስ እናንብብ፡
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ለሚሆን ግዜ ርእዮተ ዓለማዊ ፅንፈኞች፣ ከፖለቲካዊ አድማስ ከሁለቱም አቅጣጫ የሆኑ፣
በህትመት ሚድያው ሰፊ ሽፋን ያገኙ ክስተቶችን ለምሳሌ ከካስትሮ ጋር መገናኘቴን ሰበብ በማድረግ የሪክፌለር ቤተሰብ በአሜሪካ
ፖለቲካዊ እና እኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ሰፊ ተፅእኖ እንዳለን አድርገው ይወነጅሉና፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኛ ለዩናይትድ ስቴትስ ከሚበጁ ተግባራት ተቃራኒ የምንፈፅም የሚስጥር ቡድን
አባሎች ናቸው ብለው ያምናሉ፤ እኔና ቤተሰቤን “ዓለም-አቀፋውያን” እና ከሌሎች ጋር በዓለም ዙርያ የበለጠ የተዋሃደ ሉላዊ ፖለቲካዊና
ኢኮኖሚያዊ ስርአት -እንደውም ዓንድ አለም ለመገንባት የምናሴር አድርገው ይወነጅሉናል፡፡ ክሱ ይህ ከሆነ፣ ጥፋተኛ ነኝ፣ በዚህም
ደሞ እኮራለው፡፡” (David Rockefeller, Memoirs)
እነዚህ ቤተሰቦች
የሚወነጀሉት እንዲህ በቀላሉ ሳይሆን ከናዚዎች፣ ከሶቭየቶች እና ቻይናዎች ጋር ከኢራን ጋር ሳይቀር ያላቸውን የቢዝነስ ትስስርና
ከነዚህና ሌሎችም የስጋት ምንጭ ከሆኑ አሸባሪዎችና ሰብአዊ መብት የማያውቁ አምባገነኖች ጋር ያላቸው የስራ ግንኙነት የሚያደርጉላቸው
የቴክኖሎጂ ሽግግር ሁላ በተለያዩ መፅሃፍት ይፋ የተደረገ ያደባባይ ሚስጥር ስለሆነ ነው፡፡
መደምደምያ
ታሪኩን በያዘው
ሰው ማንነት ላይ አስተባባይ ወይስ ሂስ ሰጪ መሆኑ ላይ
በመመስረት የኢሉሚናቲ ታሪክ በተለያዩ ሰዎች እጅ ሲታገድ፣ ሲጋለጥ፣ ሲጣጣል፣ ሲጋነን ኑሯል፡፡ ሁሌም ሚስጥራዊ ስለሆነ ቡድን
ሙሉ እውነቱን ለማግኘትከባድ ነው፣ እውነቱን ከፈጠራው ለመለየትም ብዙ ጥረትና የመገምገም ብቃት ይጠይቃል፡፡ ይህን ማህበር
በተመለከተ ያለውን ጥያቄ በሙሉ መመለስ ባይቻልም እዚህ ግን ዋና ነጥቦቹን ለመዳሰስ ሚክረና፡፡
የዛሬም ፖለቲካዊ
መስክ በዉሻፕት ግዜ ከነበረው እጅጉኑ ይለያል፡፡ ሆኖም ግን ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ የባቫርያ ኢሉሚናቲዎች
የቫቲካንን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጭቆና ለመታገል ሲለፍፉ የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ ደሞ አዲስ የጭቆና ስልት እየተዘረጋ
ነው፡፡ የተለያዩ ዲሞክራሲዎች ወደ አንድ ዓለም መንግስትነት ሲዋሃዱ፣ የግላዊ ሚስጥራዊነት መብትና የነፃነት መብት በደህንነት
ጥያቄና በአዲስ የቁጥጥር ቴክኖሎጂ ሲተኩ፣ ትምህርት ቤቶች ብሱል አስተሳሰብን የሚያሽመደምድ ስርአት ሲከተሉ፣ ሚስጥራዊ
ዘመቻዎች ከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰት ሲያስከትሉና በሰላማዊ መንገድ ራስን የመግለፅ መብት በፖሊሳዊ አገዛዝ ከባድ እርምጃዎች
ሲኮላሽ ባለም አቀፍ ደረጃ የዚህ መሰል አዲስ የጭቆና ስርአት እየመጣ እንዳለ መገመት አያስቸግርም፡፡ የኢሉሚናቲ ስራዎችና
ሃሳቦች የእውነት የምእራቡን አለም ከቫቲካን ጭቆና ነፃ ያወጡ ናቸው ወይስ በእግሩ ተተክተው ያስቀጠሉ ናቸው?
“አናሳዎቹ፣
አሁን ያሉት ገዢ መደቦች፣ ትምህርት ቤቶቹና መገናኛ ብዙሃኑ ቤተክርስትያኑም ጭምር፣ የራሳቸው ነው፣ በጣታቸው ስር ነው፡፡ ይህ
የብዙሃኑን ስሜት እንዲያደራጁና እንዲያወዛውዙ ያስችላቸዋል፣ እናም ብዙሃኑን መሳርያ ያደርጓቸዋል፡፡” አልበርት አንስታይን http://antiglobalconspiracy.blogspot.com/2012/05/blog-post_14.html
ፅሁፉ አስደስቶህ ስለተጋራኸው የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ፡፡ ተጨማሪ ፅሁፎች ለብሎግህ ተከታታዮች ይሆኑ ዘንዳ የኔን ብሎግ ለመጥቀስ እወዳለው፡ http://antiglobalconspiracy.blogspot.com/ አመሰግናለው፡፡
ReplyDelete