Thursday, May 3, 2012

አቡነ አብርሃምን ሳውቃቸው

http://www.danielkibret.com/2011/11/blog-post_14.html?spref=blዳንኤል ክብረት
እኔ እና አቡነ አብርሃም የምንተዋወቀው ገና ወደዚህ መዓርግ ሳይመጡ የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሳይሆኑ፣ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ ሲማሩ ነው፡፡ ይበልጥ ያወቅኳቸው ግን ብዙ በሠሩበት እና ማንነታቸውንም ባስመሰከሩበት በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል አለቃነታቸው ነበር፡፡
የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ትምህርት ቤት ሲከፈት ከመድኃኒት ዘዋለ እና ከዳግማዊት ግርማይ ጋር የት/ቤቱ ቦርድ ሆኜ ሠርቼ ነበር፡፡ አቡነ አብርሃምን በሚገባ ያወቅኳቸው ያኔ ነው፡፡ እንደ አለቃ ይመራሉ፣ እንደ ባለሞያ ይሞግታሉ፣ እንደ አባት ይጋብዛሉ፣ እንደ ወንድም ስንጠፋ ይፈልጋሉ፣ እንደ ኃላፊ ይከታተላሉ፡፡
ትምህርት ቤቱን ለመስከረም ለማድረስ የነበረን ጊዜ ከሦስት ወር የማይበልጥ ነበር፡፡ ተማሪ መዝግበን፣ መምህር ቀጥረን፣ መዋቅር ዘርግተን፣ ቁሳቁስ አሟልተን፣ የትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝተን ለማጠናቀቅ ሦስት ወር፡፡ መቼም በቦታው እርሳቸው ባይኖሩ ኖሮ ይሳካ ነበር ብዬ ለመገመት ይቸግረኛል፡፡
ሁሌም የማደንቀው አንድ አመለካከት አላቸው የተሻለ ሃሳብ ያመጣ ያሸንፋቸዋል፡፡ በስብሰባችን ላይ እርሳቸው አስተዳዳሪ መሆናቸውን እንኳን እኛ እርሳቸው ራሳቸው አያስታውሱትም ነበር፡፡ ክርክር ነው፣ ሙግት ነው፣ የተሻለ ነገር አምጡ ነው፡፡ በመጨረሻ የተሻለ ነገር ያለው ያሸንፋል፡፡ የርሳቸውን ሃሳብ የጣልንበት ብዙ ጊዜ ነበር፡፡ አንድም ቀን ግን ቅር ብሏቸው ወይንም አለቅነታቸውን ተጠቅመው ድምፅን በድምፅ ሽረውት አያውቁም፡፡
ሌላም የሚገርመኝ ጠባይ ነበራቸው፡፡ የሚሠራ ሰው ካገኙ ሥልጣናቸውን ጭምር ለዚያ ሰው ለማስረከብ ምንም አይቆጫቸውም፡፡ የሚያምኑት ሰው የሚሠራን ሰው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ የምሰማው አንድ ነገር ነው፡፡ «እናንተ የምትችሉትን ሥሩ፤ ሰዎች እኔን ሲጠይቁኝ አላውቀውም እንዳልል ግን ምን እንደ ምትሠሩ ንገሩኝ፤ ብታጠፉ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ»ÝÝ በዚህ አስተሳሰብ ባይሆን ኖሮ ዛሬ አፍ አውጥቶ ሥራቸውን የሚመሰክረው የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ትምህርት ቤትን መሥራት ቀርቶ ማሰብ አይቻልም ነበር፡፡


አቡነ አብርሃምን በአሜሪካ የተሳካ ሥራ እንዲሠሩ ያደረጓቸው እነዚህ ሁለት ጠባዮቻቸው ከሌላው ዋና እና ብዙዎቻችን ካጣነው ጠባይ ጋር ተደምሮ ነው፡፡ አቡነ አብርሃም እንደ ግብጻዊው ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ለቅዳሴ እና ለሌሊት ጸሎት ልዩ ትኩረት አላቸው፡፡ እያመማቸው እና ሐኪም እየከለከላቸው እንኳን ሰዓታት፣ ኪዳን፣ ሰርክ ጸሎት እና ቅዳሴ አያስታጉሉም፡፡ እኔ በአጭር የሕይወት ታሪኬ ዲያቆንም፣ ካህንም፣ ጳጳስም ሆኖ ያገለገለ አባት አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
ክብርን ማዋረድ እና በሰዎች ዘንድ መተቸት የሚሉትን ነገሮች ሁሉ ለታላቁ የጸሎት አገልግሎት ሠውተው እንደ ዲያቆን «ተንሥኡ» ብለው ሠርክ ጸሎቱን ያደርሱ ነበር፡፡ ብቻቸውን ተነሥተው ለኪዳን ይገሠግሡ ነበር፡፡ ዲያቆናቱ ሲጠፉ ቤተ ልሔም ይወርዱ ነበር፡፡ ምንጣፍ ለማስተካከል፣ መጋረጃ ለመትከል፣ ዕቃ ለማሰናዳት ሲነሡ ጳጳስ መሆናቸው ትዝ አይላቸውም፡፡ አገልግሎቱ እንጂ፡፡
የአቡነ አብርሃም ድፍረት ከአቋም ጋር ነው፡፡ አዲስ አበባ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ መጥተው እያለ በፓትርያርኩ እግድ የትም ቤተ ክርስቲያን እንዳያስቀድሱ፣ በኋላም ከሀገር እንዳይወጡ ብዙ ጫና ነበረባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ እርሳቸው የሚያውቁት ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን «የፓትርያርኩን ስም ካልጠራችሁ ከእናንተ ጋር ኅብረት የለኝም» የሚለው አቋማቸው አልተቀየረም፡፡ ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ እንደሚሉት እንዳንዳንዶቹ ጊዜ እና ሁኔታ አይተው ቢለዋወጡ ኖሮ ተለዋዋጮቹ ያገኙትን ሁለት ሀገረ ስብከት አያጡትም ነበር፡፡
አቋም አቋም ነው፡፡ በችግሮች እና በሁኔታዎች አይለወጥም፡፡ አቋም የሌለው ሃይማኖት ሊኖረው አይችልም፡፡ ከአሥር አብያተ ክርስቲያናት በላይ በእናት ቤተ ክርስቲያን ስም እንዲጠቃለሉ ያደረጉት በዚህ አቋማቸው ነበር፡፡ «ከሕዝብ ከሚጣሉ ይህንን አቋምዎን ይተውት» ሲባሉ «ከእግዚአብሔር ከመጣላት ከሕዝብ መጣላት ይሻላል» ይሉ ነበር፡፡
በአሜሪካን ሀገር ታላላቅ ሥራዎች እየሠሩ የሚገኙ ሦስት ታላላቅ ማኅበራት አሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የሰንበት /ቤቶች አንድነት እና ማኅበረ በዓለ ወልድ፡፡ በተለይም የኋለኞቹ ሁለቱ በራሳቸው መዋቅር ነበር የሚጓዙት፡፡ እነዚህን ማኅበራት ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን መሥመር ለማስገባት ከወጣቶቹ ጋር በመከራከር፣ በማሳመን እና አብረውም በመሥራት ያደረጉትን ተጋድሎ ሳስበው አቋም እና ሃይማኖት ያለው አባት ካገኘ ወጣቱ የት ሊደርስ እንደሚችል ይታወሰኛል፡፡
በተገኘው አማራጭ ሁሉ እየተጓዙ በጉባኤያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ መሥመር ያልያዘ መስሎ በተሰማቸው ነገር ሁሉ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ ጉባኤያቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ የመውጫ መንገድ ያመለክታሉ፡፡ ራሳቸውን እንደ አንድ ተሰብሳቢ ቆጥረው ይከራከራሉ፣ እንደ አባት ይመክራሉ፣ እንደ ወንድም ያበረታታሉ፡፡
ትዝ ይለኛል የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ሲቋቋም እርሳቸው የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ዴንቨር ተደርጎ በነበረው የሰንበት /ቤቶች ጉባኤ ላይ የወጣቱ መንገድ ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ሁላችን እንፈራው የነበረውን አቋም ሠነዘሩ፡፡ ክርክር ተፈጠረ፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ሆነው መጓዝ እንዳለባቸው በድፍረት ተከራከሩ፡፡
ከጉባኤው መልስ በዘማሪት ፋንቱ ወልዴ ቀስቃሽነት የተሰባሰቡ ወጣቶች የአቡነ አብርሃምን ሃሳብ ይዘው ተነሡ፡፡ በተለይም ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እያሉ ከፍተኛው ችግራቸው ማረፊያ ነበር፡፡ ይህ ነበር ወጣቶቹን ያንገበገባቸው፡፡ አባቶቻችን በልመና ቤት አያርፉም፡፡ መንበረ ጵጵስና ያስፈልጋቸዋል አሉ፡፡ ሌላም ችግር ነበር፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ እና በአካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር የተሠራ ቤተ ክርስቲያን አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚቀድሱበት ቤተ መቅደስ አልነበራቸውም፡፡ አንዳንዶቹም ፖለቲካውን ፈርተው እንዳይመጡብን ብለው ወስነው ነበር፡፡
 ይህንን የወጣቶች ሃሳብ ሲሰሙ አቡነ አብርሃም ከኒውዮርክ ወደ ዲሲ በአውቶቡስ መጡ፡፡ በወይዘሮ ሐረገ ወይን ቤት ከወጣቶቹ ጋር ውይይት አደረጉበት፡፡ መቼም ወጣት የያዘው ነገር ኃይል እንጂ አቋም ለማግኘት ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ወጣቶቹ በልዩ ልዩ ሃሳብ ሲላጉ ከኒውዮርክ በአውቶቡስ እየተመላለሱ መክረዋል፣ አስተምረዋል፣ አሠርተዋልም፡፡ ጉባኤያት በተደረጉ ቁጥር ሳይሰለቹ ይገኙ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ከገለልተኞች፣ በሌላም በኩል ከስደተኞች፣ ሲብስ ደግሞ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ነን ከሚሉ ዘረኞች የደረሰባቸውን ጫና ሁሉ ተቋቁመው በስም ብቻ የነበረውን ሀገረ ስብከት በሕግ እንዲቋቋም፣ መንበረ ጵጵስና እና የመንበረ ጵጵስና ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረው አድርገዋል፡፡
ከኒውዮርክ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከመጡ በኋላ አናጺ ሆነው መንበር እየሠሩ፤ እንደ ልብስ ሰፊ መጋረጃ እያዘጋጁ፣ እንደ አካውንታት ሂሳብ እየሠሩ፣ እንደ ፕሮግራም መሪ ገንዘብ እንዲዋጣ እያደረጉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡ የአሜሪካ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጳጳሳትን ሲፈትሹ ክብር በሚነካ ሁኔታ ነው፡፡ ይህንን የፈታሾች ሥርዓት አልበኛነት ሊታገሡት ባለመቻላቸው የአንድ ቀን መንገድ ያህል በመኪና እየተጓዙ ነው አያሌ ሥራዎችን ያከናወኑት፡፡
አቡነ አብርሃም ከዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ወደ ሐረር እንዲዛወሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢኖርበትም ዋናው ምክንያት ግን የአቋም ሰው መሆናቸው ነው፡፡ የአበው ሊቃነ ጳጳሳት በር ሲደበደብ እና፣ አቡነ ሳሙኤል ከሥርዓት ውጭ ሲታገዱ «ይህ ከሥርዓት ውጭ ነው መታረም አለበት» ብለዋል በድፍረት፡፡ ተሐድሶ የለም የሚል ደብዳቤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ሲደርሳቸው «ተሐድሶማ አለ፤ በዓይናችንም አይተነዋል» ብለው ነው በአደባባይ የተናገሩት፡፡ ከሀገረ ስብከት በላይ የውጭ ግንኙነት ቢሮ ሲቋቋም ከማንም ቀድመው ነው ስሕተት ነው ያሉት፡፡ በመጨረሻም «የሲኖዶሱን ውሳኔ ባልስማማበትም አክብሬ ወደ ታዘዝኩበት እሄዳለሁ» ያሉትም የአቋም ሰው በመሆናቸው ነው፡፡
አሜሪካ አቡነ አብርሃምን አጣች እንጂ አቡነ አብርሃም አሜሪካን አያጧትም፡፡ ለአንድ ሐዋርያ ሀገሩ ሁሉም ነው፡፡ ምናልባትም ሰው ካልሄደ አይመሰገንምና ከእርሳቸው በኋላ የሚመጣው ሰው እርሳቸውን የሚያስመሰግን ይሆናል፡፡ «ትሻልን ሰድጄ.....» አይደል የሚባለው፡፡
አሁን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ሊቀለበስ ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ከአቡነ አብርሃም ይልቅ ከባዱ ቀጣይ ዕዳ ያለው በሲኖዶሱ እጅ ነው፡፡ አቡነ አብርሃምማ ከአሜሪካኖች ይልቅ የሐረሮች ጸሎት በልጧልና ሐረር ሄደውም ሥራ ይሠራሉ፡፡
መልካም የአገልግሎት ዘመን
ዳንኤል ክብረት

No comments:

Post a Comment