Wednesday, May 2, 2012

ፍቅር እና ሀገር

              

ዳንኤል ክብረትhttp://www.danielkibret.com/2012/04/blog-post_20.html

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌምን ለመጀመርያ ጊዜ ለማየት መጥቼ ነበር፡፡ ስመለስ አውሮፕላኑን የሞሉት ቤተ እሥራላውያን ነበሩ፡፡ በመካከሉ አንዱን ሽማግሌ «የት እየሄዳችሁ ነው ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡
«ወደ አዲስ አበባ» አሉኝ፡፡
 «ምነው አልቀበል አሏችሁ እንዴ» ስል መልሼ ጠየቅኳቸው፡፡
«ኧረ ከሄድን ስድስት ዓመታችን ነው» አሉኝ፡፡
«ታድያ ለምን ትመለሳላችሁ»
«ዋንዛዬ ጠበል ልንነከር ነው»
ዋንዛዬ ጠበልን ዐውቀዋለሁ፡፡ ደቡብ ጎንደር የሚገኝ ፍል ጠበል ነው፡፡
«እናንተ ቤተ እሥራኤል አይደላችሁ እንዴ እንዴት ዋንዛዬ ጠበል ትሄዳላችሁ»

«ብንሆንስ የኖርንበት አይደል፤ የኖርንበትን ልንተወው ነው» ተገርመው ነበር የመለሱልኝ፡፡
እውነታቸውን ነበር፡፡ መልካቸው፣ጠባያቸው፣ ባህላቸው፣ አምሮታቸው፣ ሥነ ልቡናቸው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አንድ ሊቅ አንድ ጊዜ እንዲህ ብለው ጠይቀው ነበር፡፡
«ሰው ነው በሀገር ውስጥ የሚኖረው ወይንስ ሀገር ነው በሰው ውስጥ የሚኖረው?»
አንዳችን ይህንን ሌሎቻችን ደግሞ ያንን መለስን፡፡

እርሳቸው ግን እንዲህ አሉን «መጀመርያ ሰው በሀገር ውስጥ ይኖራል፡፡ ይህ ቀላሉ ነገር ነው፡፡ የመወለድ ጉዳይ ነው፡፡ የፈቃድ ጉዳይ ነው፡፡ የአሠራር ጉዳይ ነው፡፡ የመታወቂያ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ከዚያ በኋላ የሚመጣው ነው፡፡»
«ከዚያ በኋላ ምን ይመጣል
«ከዚያ በኋላ ግን ሀገር በሰው ውስጥ ትኖራለች፡፡ ይህችን ሀገር በሰው ልብ ውስጥ የሚተክላት ፍቅር ነው፣ ባህል ነው፤ ቤተሰብ ነው፤ እምነት ነው፤ ታሪክ ነው፤ ከዚያም በላይ ደግሞ አንዳች ሁላችንም የማናውቀው ኃይል ነው፡፡ እውነተኛ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ሀገራቸው በእነርሱ ልብ ውስጥ የምትኖር ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች የትም ይኖራሉ፡፡ ሀገራቸው ግን በልባቸው ውስጥ ናት፡፡
«ሰውን ከሀገር ማስወጣት ቀላል ነው፡፡ የኃይል ጉዳይ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ የሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ የፍርድ ጉዳይ ነው፡፡ የዐቅም ጉዳይ ነው፡፡ ሀገርን ከሰው ልብ ውስጥ ማውጣት ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ ማንም ባለ ሥልጣን፣ ማንም ባለ ጉልበት፣ ማንም ባለ ጊዜ፣ የሚችለው አይደለም፡፡
«አንዳንዴ ራሱ ሰውዬው እንኳን አይችልም፡፡ እነዚህ ዘፋኞች ሲዘፍኑ «ሕመሜ» የሚሉትን ነገር ታውቃላችሁ? የሚወዱትን ነገር «ሕመሜ» ይሉታል፡፡ ተመልከቱ ያንን ነገር ይወዱታል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ሲያስቡት ያማቸዋል፡፡ ሊጠሉት አልቻሉም፡፡ ሊተውት አልቻሉም፡፡ የተውት እና የረሱት ይመስላቸዋል፡፡ ግን ደግሞ ሲያስቡት ያማቸዋል፡፡ ነገሩ ከደማቸው እና ከነፍሳቸው ጋር ተዋሕዷልና መንቀል ይከብዳቸዋል፡፡ ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ እየወጣ ያስቸግራቸዋል፡፡ ስለዚህ «ሕመሜ» ይሉታል፡፡ ሰው ሲያምመው ያለቅሳል እንጂ እንዴት ይዘፍናል? የሚያስዘፍን ሕመም አለ ማለት ነው፡፡
«ሀገርም ለአንዳንዶች እንዲህ ናት፡፡ የሚዘፍኑላት ሕመም ናት፡፡ ነቅለው ሊያወጧት ወይንም ተክለው ሊያጸድቋት ያልተቻለቻቸው ሕመም፡፡»
እኒህ ሊቅ እውነታቸውን ነው፡፡ ሂዱ ግቡ ቴሌ አቪቭ፣ የእሥራኤል የፖለቲካ ከተማ፡፡ አያሌ ቤተ እሥራኤላውያን ሠፍረዋል፡፡ እነርሱ ራሳቸው ትንሿ ጎንደር ይሏታል፡፡ እንኮየ መስክን ጎንደር ላይ ታውቁታላችሁ? ዋናው የጠላው ሠፈር፡፡ አዝማሪ ሲያቀነቅን የሚያመሽበት ሠፈር፡፡ እዚህ ቴሌ አቪቭ አለላችሁ እንኮየ መስክ፡፡
እናንተ ይኼ ይገርማችኋል፡፡ ከጠላ ቤት አጠገብ ጣሳ ተተክሎ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? ጎንደር እንኮየ መስክ እንዳይመስላችሁ፡፡ እዚህ በሰው ሀገር እሥራኤል ቴሌ አቪቭ ውስጥ ነው የምላችሁ፡፡ እነዚህ ቤተ እሥራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወጥተው መጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ ልቡና ልትወጣ አልቻለቸም፡፡
በሠለጠነው የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አውራ ጎዳና ላይ በቆዳ በተሠራ አንቀልባ፤ ያውም በዛጎል በተጌጠ ልጇን አዝላ የምትጓዝ እናት ታያላችሁ፡፡ እርሷ እምነቷ ይሁዲ እንጂ ልቧ ኢትዮጵያዊ ነውኮ፡፡ ግቡ ወደ ቤተ እሥራኤላውያን መንደር፡፡ የሚል ድምጽ ወደ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት አካባቢ ትሰማላችሁ፡፡ ጠርጥሩ እስኪ ምን ይመስላችኋል? ቡና ተቆልቶ እየተወቀጠኮ ነው፡፡ ከመንገድ ላይ የሚገዛ ቡና ንክች የማያደርጉ አያሌ ቤተ እሥራኤላውያን አሉ፡፡
እንዲያውም ዛሬ በቤተ እሥራኤላውያን ሬዲዮ ጣቢያ በእሥራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሕላዌ ዮሴፍ ቀርበው ነበር፡፡ ቤተ እሥራኤላውያንን እያስጨነቀ ያለውን ጥያቄ ሊመልሱ፡፡ የምን ጥያቄ ይመስላችኋል?
«እንጀራ ካልበላሁ ምኑን በላሁት» የሚሉ በመቶ የሚቆጠሩ ወገኖች እዚህ አሉን፡፡ የሚያሳስባቸው የጤፍ ጉዳይ ነው፡፡ ጥያቄያቸው የእንጀራ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ትንሿ ጎንደር ብቻ ሳይሆን በየቤቱ የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ የሚጠምቁ ባለሞያዎች ሞልተዋል፡፡ እንዲያውም አንዷ ባለሞያ የጠመቁት ጠላ በጉዟችን መሐል ቀርቦ የአዲስ አበባ እናቶች ጉድ ጉድ ሲሉለት ነበር፡፡
አንዲት እናት እንዲያውም «እነዚህን የመሰሉ ወይዛዝርት እዚህ መጥተው ነዋ ሀገር ቤት ጠላው አልጥም ያለን» ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ምን ጠላውን ብቻ፡፡ ብርሌ የሚያስም ጠጅ የሚጥሉም ሞልተዋል፡፡ ታድያ ምን ያደርጋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሞያ ተሰልፎ ዶሮው በነጭ ጤፍ እንጀራ ካልቀረበ ነገር ተበላሸ፡፡
«ጋዜጠኞቹ እንዴው የጤፍ ጉዳይ ምን ይሻላል? እዚህ እንጀራ ሳይበሉ ውለው የማያድሩ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት ሊያደርግልን ይገባል» ሲሉ ነበር፡፡
እነዚህን ቤተ እሥራኤላውያን ከመቀመጫቸው አስፈንጥሮ የሚያስነሳቸው የእሥራኤልን ሀገር ዜማ ሲሰሙ እንዳይመስላችሁ፡፡
«እምየ ጎንደር ጎንደር ጎንደር
የፋሲል ከተማ የቴዎድሮስ ሀገር» የሚለውን የሰሙ ጊዜ ነው፡፡ ያን ጊዜ አንገት ይወልቃል፤ ትከሻ ተፈታትቶ ይቀመጣል፤ ወገብ በነጠላ ሸብ ይደረጋል፡፡ ሽልማት ይጎርፋል፡፡
ሀገርን ከልብ ማውጣት ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ ሀገሮች ተበትነዋል፡፡ ከሀገራቸው ወጥተው የሚኖሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ¯ እንዳሉን የሚገምቱ አሉ፡፡ ከአብዛኞቹ ልብ ውስጥ ግን ሀገራቸው አልወጣችም፡፡
ታላቁ አባት አትናቴዎስ ከባዛንታይናውያን በደረሰበት ጥቃት በተደጋጋሚ የእስክንድርያን መንበር እየተወ ተሰድዶ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሮም ተገኝቶ በነበረ ጊዜ የሮሙ ሊቀ ጳጳስ ከእስክንድርያ በመባረሩ ማዘናቸውን ገለጡለት፡፡ እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው «እኔን ከእስክንድርያ ማስወጣት ቀላል ነው፡፡ ከባዱ እስክንድርያን ከእኔ ልብ ውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስክንድርያ ሩቅ አይደለችም፡፡ እስክንድርያ እኔ ልብ ውስጥ ናት፡፡ እኔ የማዝነው ከእስክንድርያ ሲያስወጡኝ አይደለም፡፡ እስክንድርያ ከእኔ ልብ ውስጥ ከወጣች ነው» ነበር ያለው፡፡
በአሁኑ ጊዜ አራት ዓይነት ኢትዮጵያውያን አለን፡፡
  1. ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፤ ኢትዮጵያም በእነርሱ ውስጥ ያለች
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ልዩ ናት፡፡ በሀገራቸው ውስጥ ሆነው፣ ችግሯን እና መከራዋን ሁሉ አብረው ተቀብለው፤ ቢያዝኑም ሳይማረሩባት የሚኖሩ ናቸው፡፡ አቡነ ሺኖዳ «በአካል ካለችው ግብጽ በልባችን ውስጥ ያለችው ግብጽ ትበልጣለች» እንዳሉት በእነዚህ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያም ታላቅ ናት፡፡ በቀበሌው፣ በአስተዳደሩ፣ በአመራሩ፣ በአሠራሩ፣ በኢኮኖሚው፣ በኋላ ቀርነቱ ወዘተ ምክንያት በሚደርሰው ነገር አይለኳትም፡፡ እዚህ በዓይናቸው የሚያዩት ገጽታ በውስጣቸው ያለችውን ኢትዮጵያ ገጽታ አይቀይርባቸውም፡፡ የእነርሱ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት፤ ኩሩ ናት፤ ጀግና ናት፤ ነጻ ናት፤ ውብ ናት፤ ፍቅር ናት፤ ሥልጡን ናት፡፡ ሲሠሩ፣ ሲደክሙ፣ ሲያለሙ፣ ሲሠው፣ ሲከፍሉ፣ በልባቸው ላለቺው ኢትዮጵያ ነው፡፡ በሚያዩዋት ኢትዮጵያ እንጂ በልባቸው ባለቺው ኢትዮጵያ አይማረሩም፡፡
  1. ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፣ ኢትዮጵያ ግን በእነርሱ ውስጥ የሌለች
እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ አንዳችም የኢትዮጵያ ጠባይ፣ ባህል፣ ፍቅር፣ ክብር፣ አመል፣ ስሜት፣ ወኔ፣ ቅንዐት በልባቸው ውስጥ የለም፡፡ ለእነርሱ ኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ብቻ ናት፡፡ ቦታ ብቻ ናት፡፡ በሰሜን ኤርትራ፣ በደቡብ ኬንያ፣ በምዕራብ ሱዳን፣ በምሥራቅ ሶማልያ እና ጂቡቲ የሚያዋስኗት ሀገር ብቻ ናት፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ኢትዮጵያ ብትወድቅ ብትነሣ፣ ብትሞት ብትድን፤ ቢያልፍላት ባያልፍላት፣ ብታድግ ብትደኸይ አይገዳቸውም፡፡ ሊጠቅሟት ሳይሆን ሊጠቀሙባት ብቻ ይፈልጓታል፡፡ ስለ እነርሱ እንድትኖር እንጂ ስለ እርሷ እንዲኖሩ አይፈልጉም፡፡ ለእርሷ አይሠውም፤ ለእነርሱ ግን ይሠውዋታል፡፡
  1. ከኢትዮጵያ የወጡ፣ ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ ልብ ያልወጣች፣
እነዚህ ደግሞ ወደውም ሆነ ሳይወዱ ከሀገር የወጡ ናቸው፡፡ በአካል ከሀገር ርቀዋል፡፡ በልባቸው ግን ኢትዮጵያን ፀንሰዋል፡፡ ደማቸው፣ ጠባያቸው፣ እምነታቸው፣ ዐመላቸው፣ ባህላቸው፣ ስሜታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ስሟን ሲሰሙ አንዳች ነገር እንደ ኤሌክትሪክ ይነዝራቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን፣ ቤታቸውን፣ አቆጣጠ ራቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ጸሎታቸውን ሁሉ ኢትዮጵያኛ አድርገውታል፡፡ ለእነርሱ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ቀን ነፍሳቸውም ሥጋቸውም እዚያው ኢትዮጵያ ትኖራለች፡፡ ቢሞቱ እንኳን ሥጋቸው እንዲመለስ ይፈልጋሉ፡፡
  1. ከኢትዮጵያ የወጡ፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ልብ የወጣች
እነዚህ ደግሞ የሚኖሩትም ውጭ ነው፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ወጥታለች፡፡ ምናልባትም መልካቸው ብቻ ካልሆነ በቀር አንዳችም ከሀገራቸው ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር በዲኤን እንኳን ላይገኝ ይችላል፡፡ ለእነርሱ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ አንዲት ሀገር ናት፡፡ በቃ፡፡ ብትኖር ብትሞት ስሜት አይሰጣቸውም፡፡ አይኖሩባትም፤ አትኖርባቸውም፡፡ «ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ» የሚል ምሕላ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያን ከልባቸው ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸው ልብ አንዳትገባም አድርገዋታል፡፡
በዓለም ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ሁለት ቃላትን መተርጎም ከባድ ነው ይባላል፡፡ «ፍቅር እና ሀገር»፡፡ ልብ እንጂ ቃል አይተረጉማቸውምና፡፡
እኛስ ከየትኞቹ ወገን ነን?```

ዳንኤል ክብረትhttp://www.danielkibret.com/2012/04/blog-post_20.html

1 comment: