መጀመርያ ወደ ሱዳን ኤምባሲ ሄዳችሁ ሱዳን የመግቢያ ቪዛ ታወጣላችሁ፡፡ ከዚያ በጎንደር በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ትገሠግሣላችሁ፡፡ ‘የሱዳን ሕዝብ ጥሩ ነው፣ለስደተኞች ይራራል‘ ይላሉ ጣልያን የገቡት ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፡፡ እዚያ የታወቁ ሁለት አሸጋጋሪዎች አሉ፡፡ በአካል አታገኟቸውም፡፡ ስልካቸውን ከሀገር ሳትወጡ ይዛችሁ መሄድ አለባችሁ፡፡ አለበለዚያም ጣልያን የገባ ሰው ሊነግራችሁ ይገባል፡፡
አንዳች
ሰዋራ ሥፍራ ተደብቃችሁ በስልክ ታገኟቸውና የጉዞ ዋጋ እና ቀን ትነጋገራላችሁ፡፡ እነርሱም ገንዘቡን ይዛችሁ
የምትመጡበትን ቦታ እና ቀን ይነግሯችኋል፡፡ በተባላችሁት ሌሊት እቦታው ስትደርሱ እንደ እናንተ በቀጠሮ የመጡ ሌሎች
ስደተኞችን ጨምረው በጭነት መኪና ወደ ሊቢያ ድንበር ትወሰዳላችሁ፡፡ ጉዞው ሌሊት ሌሊት፣ ያውም አብዛኛው በእግር፣
ጥቂቱ ደግሞ በመኪና ስለሆነ ከሃያ ቀን እስከ አንድ ወር ይፈጃል፡፡
ሊቢያ
ድንበር ስትደርሱ የሱዳን አሸጋጋሪዎች ለሊቢያ አሸጋጋሪዎች ያስረክቧችኋል፡፡ ዋጋ ተነጋግራችሁ አሁንም ጉዞ
ትጀምራላችሁ፡፡ ግማሹን በእግር ግማሹን በፒክ አፕ መኪና፡፡ ደረቅ ዳቦ እና ውኃ ይሰጣችኋል፡፡ መንገድ ላይ የሚሞቱ
ልጆች ይኖራሉ፡፡ አሸዋውን ማስ ማስ አድርጎ በመቅበር ጉዞ መቀጠል ነው፡፡
«በእግር
ወይንም በመኪና ስትጓዝ በእንጨት የመስቀል ምልክት የተሠራበት ነገር ካየህ እዚያ ቦታ አንድ አበሻ ስደተኛ
ተቀብሯል ማለት ነው፡፡» ብሎኛል ጣልያን ያገኘሁት ልጅ፡፡ «ሰው ከታመመ እንደ በሽታው ነው፡፡ መጠነኛ ከሆነ
በድጋፍ ይሄዳል፡፡ ከባድ ከሆነ ግን ቁርጥ ወገን ያስፈልገዋል፡፡ ከቡድኑ ከተቆረጥክ ችግር ስለሚያጋጠምህ አንዳንዱ
ትቶህ ይሄዳል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን የቂርቆስ ልጆች ይተዛዘናሉ፡፡ እንዲያውም
ከቂርቆስ ልጅ ጋራ አብረው ቢሰደዱ
ቢያገኝም ያበላል ቢያጣም ያዝናል ሆዱ
ተብሎ
ተዘፍኖላቸዋል፡፡» አለኝ ሮም ያገኘሁት የአዲስ አበባው የቂርቆስ ልጅ፡፡ አዲስ አበባ ስለ ቂርቆስ ሠፈር ልጆች
አያሌ አስገራሚ እና አስቂኝ ነገሮች እሰማ ነበር፡፡ እዚህ ጣልያን ደግሞ አገር ጉድ የሚያሰኝ ገድላቸውን መስማት
ጀምሬያለሁ፡፡
ሊቢያ
ስትገቡ የተቀበሏችሁ አሸጋጋሪዎች ከትሪፖሊ አጠገብ የገጠር መንደር ውስጥ በተሠራ አዳራሽ አስገብተዋችሁ ይጠፋሉ፡፡
ከዚያ ሌሎች አሸጋጋሪዎች ደግሞ ይመጡና «ትሪፖሊ ሩቅ ስለሆነ እንድንወስዳችሁ መቶ መቶ ዶላር ክፈሉ» ይሏችኋል፡፡
ታድያ የቂርቆስ ልጆች ምን አደረጉ መሰላችሁ፡፡ የተወሰኑት ልጆች ሌሊት ተደብቀው ይወጡና እግራቸው ወዳመራቸው
ሲጓዙ ለካስ ትሪፖሊ ቅርብ ነው፡፡ ተመልሰው ይመጡና ሌሎችን ልጆች ነጻ ያወጧቸዋል፡፡ ከእነርሱ በኋላ ለሚመጡት
ስደተኞች ደግሞ ግድግዳው ላይ በአማርኛ እንዲህ ብለው ይጽፋሉ «እንዳት ሸወዱ፣ ትሪፖሊ ቅርብ ነው፡፡ ብር ስጡን
ቢሏችሁ አትስጡ፡፡ በዚህ እና በዚያ አድርጋችሁ ጥፉ» ይሄ ማስታወቂያ አያሌ ስደተኞችን ታድጓቸዋል፡፡ አይ የቂርቆስ
ልጆች፡፡ ነፍስ ናቸውኮ፡፡
ትሪፖሊ
ገብታችሁ የመርከብ ወረፋ መጠበቅ ነው፡፡ ክፉ ፖሊሶች ካገኟችሁ በመኪና ጭነው እንደ ገና ወደ ሱዳን ድነበር
ወስደው ያሥሯችኋል፡፡ እዚያ እሥር ቤቱ በጣም አሰቃቂ ነው፡፡ እዚያም ቢሆን የቂርቆስ ልጆች ካሉ መከራው
ይቀልላል፡፡ ከእሥር ቤቱ ለመውጣት የገንዘብ ጉቦ ያስፈልጋል፡፡ ያንን ደግሞ ለማግኘት ወይ አስቸጋሪ ሥራ መሥራት
ያለበለዚያም ደውሎ ከዘመድ ማስመጣት ያስፈልጋል፡፡
እዚያ
እሥር ቤት ብዙ ልጆችን ያስፈታ አንድ የቂርቆስ ልጅ ነበር፡፡ ሥራ ይወዳል፡፡ ሲጋራ፣ ብስኩት እና ሳሙና እየሸጠ
ይኖር ነበር፡፡ በዚያ እሥር ቤት ብዙ ጊዜ የቆየው ሌሎችን ሲያስ ፈታ ገንዘቡ እያለቀበት ነው ይባላል፡፡ ሌሎች
ደግሞ በሌላ ነገር ይተርቡታል፡፡ ከእሥር ቤቱ ሊወጣ በር ላይ ሲደርስ «አንድ ሲጋራ አለህ» የሚል ገዥ ሲመጣ ለርሱ
ሊሸጥ እየተመለሰ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ በአጥር ዘለሎ ሊያመጥ ሁሉም ነገር ተስተካክሎለት ነበር፡፡ ሊዘልል
አንድ እግሩን እንዳሣ «አንድ ሲጋራ አለህ» የሚለውን ሲሰማ ተመልሶ መጣ ይባላል፡፡
በቤንጋዚ
ወደብ አሻጋሪዎች እና ተሻጋሪዎች አይገናኙም፡፡ ሃያ እና ሰላሣ ሰው እስኪሞላ የሚመዘግቡ ሰዎች አሉ፡፡ የቡድኑ
አባላት ሲሟሉ ገንዘብ ይከፍሉና ወደሚሻገሩበት ወደብ ይወሰዳሉ፡፡ የመሻገሪያዋ ጀልባ ብዙ ጊዜ ከቆርቆሮ እና
ከእንጨት የምትሠራ ናት፡፡ ለአንዱ ስደተኛ አሻጋሪዎቹ የመርከቧን አነዳድ ያሳዩታል፡፡ ትምህርቱ ቢበዛ ከአንድ ቀን
በላይ አይሰጥም፡፡
ለዚያ
መከረኛ «ካፒቴን» የጀልባዋን ኮምፓስ አሥረው ካርታውን ያስረክቡታል፡፡ ምግብ እና መጠጥ ይጫናል፡፡ እንደ ጀልባዋ
ስፋት ከሃያ እስከ ሠላሳ ስደተኛ ይሳፈራል፡፡ በሌሊት የጣልያንን መብራት በሩቁ እያዩ ጉዞ ይጀመራል፡፡ አሻጋሪዎቹ
ጀልባዋ ስትነሣ ይመለሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ዕዳው የስደተኞቹ ነው፡፡
ጉዞው
እስከ አስራ ሰባት ሰዓት ይፈጃል፡፡ የአንዱ እግር ከሌላው ጀርባ ጋር ተሰናስሎ ተኮራምቶ መጓዝ ብቻ ነው፡፡ ሙቀቱ
እና ተስፋ መቁረጡ አንዳንዶችን ራሳቸውን ወደ ባሕሩ እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይም መርከቡ መንገድ ከሳተ፡፡
የሚያስጎበኘኝን
የቂርቆስ ልጅ «ለምንድን ነው ጣልያን ውስጥ የቂርቆስ ሠፈር ልጆች የሚበዙት፡፡ እንዲያውም ሮም ውስጥ የቂርቆስ
ልጆች ብቻ ያሉበት አንድ ሕንፃ አሳይተውኛል፤» አልኩና ጠየቅኩት፡፡ «ምናልባት የሱዳን ኤምባሲ ሠፈራችን ውስጥ
ስለሆነ ይሆናል በሱዳን በኩል እያቋረጥን የመጣነው» አለና ቀለደብኝ፡፡ «ቆይ ግን ለመንገዱ ብዙ ዶላር ያስፈልጋል
ሲባል ነበር የምሰማው፤ እንዴት ነው ጉዳዩ» አልኩት፡፡ «ቂርቆስ የድኻ ሠፈር ነው ብለው ስማችንን ያጠፉትኮ የቦሌ
ልጆች ናቸው፤ እነርሱ አውሮፕላን ሲያዩ ስለሚውሉ የገዙ እየመሰላቸው ነው፤ እንዲያውምኮ መንግሥት ሀብታም ገበሬዎችን
ብቻ ሳይሆን እኛንም መሸለም ነበረበት፤ የመረጃ እጥረት ነው» አለኝ፡፡
«እንዴት?»
አልኩት፡፡ «እስኪ ተመልከት እኛ የቂርቆስ ልጆች የመንግሥትን እጅ ሳንጠብቅ፤ አነስተኛ ፣ጥቃቅን ሳንል፤ ራሳችንን
በራሳችን ረድተን እዚህ መድረሳችን አያሸልመንም» አለና ሳቀ፡፡ «ሀብታም ገበሬዎች ራሳቸውን ቻሉ እንጂ የሕዝብ
ቁጥር አልቀነሱም፤ እኛ ግን ራሳችን ንም ቻልን፣ከሀገር በመውጣታችን ደግሞ የሕዝብ ቁጥር ቀነስን፡፡ ከዚህ በላይ
ምን የሚያሸልም ነገር አለ፡፡ አየህ እኛ እንደ ቦሌ ልጆች ጆግራፊን በቲቪ ሳይሆን በተግባር ነው የምንማረው»
«ደግሞምኮ የአባቶቻችንን ደም የመለስን እኛ ነን» አለኝ እየሳቀ፡፡ «እንዴት?»
«ጣልያን ባሕር አቋርጦ ሀገራችንን ወረረ፡፡ እኛ ደግሞ የአባቶቻችንን ደም ለመበቀል ባሕር አቋርጠን ሀገሩን ወረርነዋ፤ አንተ ቂርቆስኮ የጀግና ሠፈር ነው» አለና ሳቀ፡፡
«እውነት
ግን ለምንድን ነው የቂርቆስ ልጆች እዚህ የበዛችሁት?» «ምን መሰለህ ይህንን በረሃ ለማቋረጥ ከሁለት እስከ ሦስት
ወር ይፈጃል፡፡ የገንዘብ፣ የምግብ፣ የውኃ ችግር አለ፡፡ ካልተዛዘንክ በቀር ይህንን በረሃ ልታልፈው አትችልም፡፡
እኛ ደግሞ ከልጅነታችን ተዛዝነን መኖር ለምደናል፡፡ ስለዚህ እየተደጋገፈክ መጓዝ ነው፡፡ ያው እንግዲህ ባሕር
ኃይልም አየር ኃይልም እየመጣ ይቀጥላል»
«የቀድሞ
ወታደሮችም ይመጣሉ ማለት ነው» «አይ እነርሱ አይደሉም፡፡ በአውሮፕላን ጣልያን የገባው ስደተኛ አየር ኃይል
ይባላል፡፡ በባሕር የገባው ደግሞ ባሕር ኃይል ይባላል፡፡ ታድያ አየር ኃይሉ ባሕር ኃይሉን ይንቀዋል፡፡»
«ለምን?»
«ያው መከፋፈል ለምዶብን ነዋ፤ አታይም መንገድ ላይ እንኳን ጉስቁል ያለ አበሻ ካዩ ሰላም አይሉንም፡፡ ጣልያኖች
እንደሆኑ አየር ኃይልም ሆንክ ባሕር ኃይል ሚኒስትር አያደርጉህም፤ ሁሉም ያው ሲኞራ ቤት ነው የሚሠራው፡፡
«ሲኞራ ቤት ደግሞ ምንድን ነው?» «ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት ማለት ነው፡፡ እዚህ ብዙው አበሻ እንደዚያ ነው የሚሠራው፡፡ ያውም ለሴቶች እንጂ ለወንዶች ሥራ አይገኝም፡፡ ድድ ስታሰጣ መዋል ነው፡፡»
«ግን
ምን ላይ እየኖርክ ድድ ታሰጣለህ» አልኩት፡፡ «እዚህ አበሻ ከድንኳን ሰባሪነት ወደ ሕንፃ ሰባሪነት ተሸጋግሯል»
«እንዴት እንዴት ሆኖ» «ያንን ሁሉ በረሃ አቋርጠህ፤ ባሕር ሰንጥቀህ ጣልያን ስትገባ ምንም ነገር አታገኝም፡፡
ከምግብ በቀር ቤት እንኳን የሚሰጥህ የለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ መጠለያ ውስጥ ያስገቡህና በኋላ ሠርተህ ብላ ብለው
ያሰናብቱሃል፡፡ ያን ጊዜ ችግር ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ አበሻ ታድያ ይሰባሰብና በልዩ ልዩ ምክንያት የተዘጋ ሕንፃ
ያስሳል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ሁኔታውን ታይና ሃያ ሠላሳ ሆነህ በሩን ሰብረህ ትገባለህ፡፡ ከዚያ ክፍሎቹን መከፋፈል
ነው፡፡»
«ባለቤቶቹስ»
«ባለቤቶቹ ኡኡ ይላሉ፡፡ ፖሊስ ይመጣል፤ ግርግር ይፈጠራል፡፡ የሰው ልጅ ሜዳ ላይ ወድቆ እንዴት ሕንፃ ተዘግቶ
ይኖራል ብለህ ትከራከራለህ፡፡ መቼም የሰው መብት በመጠኑም ቢሆን የሚከበርበት ሀገር ነውና የሰው መብት ተከራካሪድር
ጅቶችም አብረውህ ይጮኻሉ፡፡ በመጨረሻ ታሸንፍና ትኖርበታለህ፡፡»
«መብራት እና ውኃ አይቆርጡባችሁም» ?«ብዙ ጊዜ
መብራቱን እንጂ ውኃውን መቁረጥ ያስቸግራቸዋል፡፡ የሮም ሕንፃዎች የድሮ ሕንፃዎች ናቸው፡፡ የውኃ መሥመሩ በቀላሉ
አይገኝም፡፡ መብራቱን ግን ቢቆርጡትም እንቀጥለዋለን፡፡ አንድ ልጅ እንዲያውም በዚያ ምክንያት ሥራ አግኝቷል፡፡»
«መብራት በመቀጠል?» «አዎ፤ የቤቱን መብራት
ሲቆርጡት በመንገድ ከሚያልፈው መብራት ሌሊት ቀጠለው፡፡ ፖሊሶቹ ሲመጡ ይበራል፡፡ ሄደው ከዋናው ማጥፊያ ቢያለያዩትም
ይበራል፡፡ አይተው ስለማያውቁ ግራ ገባቸው፡፡ በኋላ ከመንገዱ መብራት መቀጠሉን ሲያዩ እንዴት ሊቀጠል እንደቻለ
ማመን አልቻሉም፡፡ እና ትተውት ሄዱ፡፡ ይሄው ፏ ብሎልሃል፡፡ ልጁም ታድያ ኤሌክትሪክ ሠራተኛ ሆኖ ቀረ»
«ሴቶች ሲኞራ ቤት ይሠራሉ አልከኝ፤ ወንዶችስ ምን
ይሠራሉ?» «ወንድ ከሆንክ አልፎ አልፎ ነው ሥራ የምታገኘው፡፡ ችግር አለ፡፡ አንዱ አበሻ ሲርበው ሴት ነኝ ብሎ
ሲኞራ ቤት ተቀጥሮ ነበር አሉ፡፡» «እውነትክን ነው ወይስ ቀልድ ነው» «እኔ ሲያወሩ ነው የሰማሁት፡፡» «እሺ
ከዚያስ» «ልጁ ጢም የለውም፤ መልኩ የሴት ድምጽ ነው፡፡ እንዲያው ልጆች በሌላ ነገር ይጠረ ጥሩታል» «ምን ብለ»
«ነገርዬው የለውም ይሉታል» «እሺ»
«እና ጉልበታም ነው፤ ሥራዋን ፉት፣ ጭጭ ነበር አሉ
የሚያደርጋት፡፡ አንድ ቀን የሽንት ቤቱን በር ሳይዘጋው ረስቶት፣ ቆሞ ሽንቱን ሲሸና ሲኞራው በሩን ሲከፍት ፌንት
ወጣ አሉ፡፡ ነፍሷ ደሞዟን ሳትቀበል ከቤት ወጥታ ጠፋች፡፡ በኋላ ግን እንደዚያ ያደረገው ሥራ ስላጣ መሆኑን ሲኞራው
ሲሰማ አድንቆ ካምፓኒው ውስጥ ቀጠረው አሉ»
«ተው እባክህ፤ ይሄን የመሰለ ፊልም አይቻለሁ፤ ሲኮምኩ ይሆናል» «ኩምክና አይደለም፤ የሆነ ነው ብለውኛል»
«እሺ ይህንን ሁሉ ባሕር አቋርጦ የመጣ ሰው መጨረሻው ምንድን ነው?»
«ወይ ትመርሻለህ፣ ወይ ትፈርሻለህ፣ ወይ ትደነብሻለህ» «ምንድን ነው መመረሽ፣ ምንድን ነው መደንበሽ፣ ምንድን ነው መፈረሽ»
«ጣልያን ለመኖር የሚመጣ የለም፣ ስለዚህ ትንሽ
ገንዘብ ነገር ቆጣጥረህ ወደ እንግሊዝ ትሻገራለህ፤ ይኼ መመረሽ ይባላል፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ እዚሁ የመኖርያ ፈቃድ
አወጥተህ የተሻለ ሥራ ካገኘህ ትኖራለህ፤ ይኼ ደግሞ መፈረሽ ይባላል፡፡ ሁለቱም ካልሆነልህ ደግሞ ትጀዝብና ደንብሸህ
ትኖራለህ፡፡ ሚላኖ፣ ጣልያን
የቂርቆስ ልጅ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር...ሃሪፍ ታሪክ ነው።
ReplyDelete