የኔ ጀግና
በቀደም ዕለት ፕሮግራማችሁን ስከታተል የዓመቱን
የCNN ጀግኖች ምረጡ የሚል ማስታወቂያ በተደጋጋሚ አየሁ፡፡ ነገር ግን ምርጫው ካቀረባችኋቸው ዕጩዎች መካከል
ሆነብኝና ተቸገርኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ልመርጣት የምችላት የኔዋ ጀግና አልተካተተችምና፡፡ እናንተ ካቀረባችኋቸው
ዕጩዎች የተለየች፣ ምናልባትም ሥራዋን ባለማወቅ የተነሣ ማንም በዕጩነት ሊያቀርባት የማይችል አንዲት ጀግና አለች፡፡
የእኔ ጀግና እርሷ ነች፡፡
በ1960ዎቹ መጨረሻ የዚህች ሀገር ልጆች ጎራ
ለይተው ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ብለው ተጨፋጨፉ፡፡ ከሁለቱም ወገን እልፍ አእላፋት ልጆች ደማቸው እንደ ጨው
ተዘርቶ ቀረ፡፡ አባታችን ከቤት እንደወጣ የቀረው ያኔ ነበር፡፡
በኋላ በኋላ እንዳወቅኩት አባቴ ቀይ ሽብር
ተፋፍሞበት መንገድ ላይ ተጥሎ ኖሯል፡፡ ለእናቴ ከኀዘኑ በላይ የጎዳት አስከሬኑን ለማንሣት በየቢሮው ደጃፍ፣
በየባለሥልጣናቱ ግቢ ያየችው መከራ፣ የከፈለችው ጉቦ ነው፡፡ እንዲህ ላለው ነገር እንግዳ በመሆኗ ሰዎች ይሆናል
ያሏትን ሁሉ ታደርግ ነበር እንጂ ለውጤቱ ርግጠኛ አልነበረችም፡፡
ቀብሩ በዘመድ አዝማድም፣በጉቦም ተፈጸመ፡፡ ቀጣዩ
ኑሮ ግን በዘመድ እና በጉቦ የሚዘለቅ አልሆነም፡፡ የቤት እመቤቷ እናታችን እናትም አባትም ሆነች፡፡ ቤቱ
የሚተዳደረው በአባታችን ደመወዝ እና በእናታችን ጉልበት ነበር፡፡ አሁን የመተዳደርያውን ገንዘብ ማምጣቱም ሆነ
የቤቱን ሥራ መሥራቱም የርሷ ኃላፊነት ነበር፡፡ እኛ ልጆቿ ደግሞ እንዳናግዛት ለሥራ ያልደረስን ለመብል ያላነስን
ሕፃናት ነበርን፡፡ ለእናታችን የአባትነት ኃላፊነቱ እንጂ ወጉ እና መዓርጉ አልተረፋትም፡፡
እናታችን የመጀመርያውን ብርቱ ትግል ያደረገችው
ሕልውናዋን ለማስጠበቅ ነው፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም ያሰቡ ሰዎች የተከራየነውን ቤት መውሰድ ፈለጉና ቀበሌ ተጠራች፡፡
«አሁን ባለቤትሽ ስላረፈና አንቺም ገቢሽ አነስተኛ ስለሆነ ይህንን ሰፊ የቀበሌ ቤት ለቅቀሽ በዐቅምሽ ሌላ አነስ
ያለ ቤት ውሰጅ» ተባለች፡፡ መክፈል እንደምትችል፤ ስትቸገር ያን ጊዜ ጉዳዩን እንደምታመለክት ለማን ታስረዳው፡፡
ለመናገር እንጂ ለመስማት ዝግጁ የሆነ ባለሥልጣን ማግኘቱ ነበር ከባዱ፡፡ ያውምኮ የቤቱ ኪራይ ሃያ አምስት ብር
ነበር፡፡ መቼም አንዳንድ ደግ ሰው በየዘመኑ አይጠፋም፡፡ ከአመራሮቹ መካከል በደረሰባት ነገር ያዘኑ ሰዎች ረድተዋት
በስንት መከራ ቤታችንን ከመልቀቅ ተረፍን፡፡
በርግጥ ለእናታችን ያችን ሃያ አምስት ብር ማግኘቱም
ቢሆን ከባድ ነበር፡፡ ሥራ ለመቀጠር ስትሄድ ያ የቀይ ሽብር ታሪክ ቀድሟት ይደርስና ምክንያቱንም ውጤቱንም
በማታውቀው ነገር፣ የርሷ ፍላጎት እና ተሳትፎ ይኑርበት አይኑርበት ባልተጣራ ነገር አዝና ትመለሳለች፡፡ ከሁሉም
የሚከብዳት ግን ባሏ የሞተባት ሴት ሁሉ ለሥጋዊ ነገር ትንበረከካለች ብለው በሚያስቡ ወንዶች የሚመጣባት ፈተና
ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሥራ ፈተናው ቤታቸው ይሰጥ ይመስል ቤታቸው ይቀጥሯታል፡፡ ሌሎቹ የመሥሪያ ቤቱ ቢሮ ጠቧቸው
ሆቴል የተከራዩ ይመስል ሆቴል ይቀጥሯታል፡፡
እንጀራ ነውና መቅረት እየከበዳት፣ ችግሩን
ታውቃለችና መሄዱም እየዘገነናት ለኛ ስትል አንድ ሁለት ጊዜ ሞከረችው፡፡ ነገር ግን የተፈለገው ዕውቀቷ እና ጉልበቷ
ሳይ ሆን ሴትነቷ መሆኑን ስታውቅ እንደ አራስ ነበር ተቆጥታባቸው፣ እንደ አንበሳ አግሥ ታባቸው ትመጣና ቤት ገብታ
ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡ ጸጋዬ ገብረ መድኅን «ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው» ብሎ ነበር፡፡ ወንድ ልጅ
ብቻ አይደለም ብቻውን የሚያለቅሰው፡፡ አባትም እናትም ሆና ልጆቿን የምታሳድግ ጀግና እናትም ብቻዋን ነው
የምታለቅሰው፡፡ ልጆቿ እንዳይረበሹባት ልጆቿ ፊት አታለቅስም፡፡ መጠቃቷ እንዳይታ ወቅበት በአደባባይ አታለቅስም፡፡
ብቻዋን ነው የምታለቅሰው፡፡
ወርቆቿን ሸጠች፣ጥሩ ጥሩ ልብሶቿን ሸጠች፣ የቤት
ዕቃዎቿን ሸጠች፣ በደኅና ጊዜ የገዛ ቻቸውን ጫማዎቿን ሳይቀር መሸጧን ከቤታችን ሲጠፉ ነበር የምናውቀው፡፡ በኋላም
እኛን ሁሉ ያሳደገችውን አንዲት አነስተኛ ሱቅ ከፈተች፡፡ እኛ ትምህርታችን እና ኑሯ ችን አልተቋረጠም፡፡ የእርሷ
ሰውነት ግን እየተለወጠ ሲሄድ ይታወቀናል፡፡ እርሷ ከኑሮ ጋር ብቻ አይደለም የታገለችው ከበሽታ ጋር ጭምር ነው፡፡
ሕመሟ እንዳይታወቅባት በውስጧ ትቋቋመው ነበር፡፡ ብተተኛ ብትተኛ እንኳን ከሁለት ቀን በላይ አትተኛም፡፡ በኋላ
በኋላ ግን በሽታውንም አሸነፈችው መሰል አያማትም ነበር፡፡
ዛሬ ዛሬ ሳስበው የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ግዥልን
ያልናትን ሁሉ ትገዛለች፡፡ አድርጊልን ያልናትን ሁሉ ታደርጋለች፡፡ አንድም ቀን አትማረርም፡፡ ከየት እንደምታመጣው
አላውቅም፡፡ እኛ ፊት እንደ ድሮው ትጫወታለች፡፡ ለትምህርታችን የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አልተጓደለም፡፡ ከየት
ነበር የምታመጣው? የሚለውን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ እንደ ጧፍ አብርታ፣ እንደ ሻማ ቀልጣ ድህነትን አሸንፋ ልጆቿን
አስተምራ ለሀገር ያበረከተች ይህች የጀግኖች ጀግና አይደለችም?
ዛሬ ዛሬ «ሃርድ ቶክ» ላይ ቀርበው ከባድ ከባድ
ጥያቄዎችን በድፍረት የሚመልሱ ተጠያቂዎች ሲያደነቁ እሰማለሁ፡፡ ባታውቋት ነው እንጂ የኔ እናት ስንት «የሃርድ
ቶክ» ጥያቄ በድፍረት መልሳለች መሰላችሁ፡፡ ያውም በቴሌቭዥን ሳይሆን በሕይወት፡፡ አባታ ችን የት ሄደ? ለሚለው
የኛ የልጆቿ ጥያቄ ሁልጊዜ መልስ መስጠት አለባት፤ ለምን ሌላ ባል አታገቢም ? ለሚለው የዘመዶቿ ጥያቄ መልስ
መስጠት አለባት፤ እንዴት እርሱ የለም ብለሽ እንዲህ እና እንዲያ ታደርጊያለሽ? ለሚለው የአባታችን ዘመዶች ጥያቄ
መልስ መስጠት አለባት፤ በብቸኝነቷ ሊጠቀሙ ለሚፈልጉ ዘለሌዎች መልስ መስጠት አለባት፤ እንዲህ ለምን አታደርጊም
እንዲያ ለምን አታደርጊም እያሉ ያለ ፍላጎቷ ሊያስኬዷት ለሚፈልጉ ጎረቤቶቿ እና ወዳጆቿ መልስ መስጠት አለባት፡፡
እና ይህች ጀግና አይደለችም ትላላችሁ፡፡ «ሀርድ ቶክ»ን ሳይሆን «ሀርድ ላይፍ»ን የተቋቋመች፡
እንዲያ ብቻዋን እየታገለች፡፡ አገር በሙሉ ድንኳን
ተክሎ ለአባቴ ልቅሶ መቀመጡን እያወቀው፣ ጀግንነቷን ግን የሚያደንቅላት አልነበረም፡፡ ከፍ እያልኩ ስሄድ
የሚያናድደኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ ሠርግ እና ተዝካር ስትጠራ በመጥሪያ ወረቀቱ ወይንም ካርዱ ላይ የአባቴ ስም
ይጻፋል እንጂ የርሷ ስም አይጻፍም፡፡ እድር የምንከፍለው፣ የቤት ኪራይ የምንከፍለው፣ መብራት እና ውኃ የምንከፍለው
በአባቴ ስም ነው፡፡ ለምን? እርሷኮ አባትም እናትም ሆና እየኖረች ነው፡፡
በሠፈራችን የአባቴ እና የእናቴ እድር የተለያየ
ነው፡፡ የወንድ እድር እና የሴት እድር፡፡ አባቴ በሕይወት እያለ እርሷ ወደ ሴት እድር እርሱ ደግሞ ወደ ወንድ
እድር ነበር የሚሄዱት፡፡ አሁን ግን አባትም እናትም ሆናለችና በሁለቱም እድር መገኘት ያለባት፤ መክፈል ያለባት
እርሷው ናት፡፡ የሴት እድር በጓዳ ሥራ መጠመዱ የተለመደ ስለሆነ እዚያ ስትሄድ እርሷም ጓዳ ገብታ ትሠራለች፡፡
የሚገርመኝ ግን የወንድ እድርተኞች የመጀመርያ ቀን ድንኳን ተክለው ድንኳን ውስጥ ከብበው ካርታ ከመጫወት ውጭ
አንዳችም ሥራ የላቸውም፡፡ እርሷ የወንድ እድር ክፍያዋን ብትከፍልም እንደ ወንድ እድርተኞች ድንኳን ውስጥ
እንድትቀመጥ የሚፈቅድላት ግን የለም፡፡ ለክፍያው እና ለጥሪው ወንድ፣ ለሥራው ግን ሴት ናት፡፡
ማኅበረሰቡ ለጀግንነቷ ዕውቅና ላለመስጠት ያላደረገው
ጥረት አልነበረም፡፡ በሴትነቷ የሚደርስባትን ጥቃት ሁሉ ችላ፤ አባትም እናትም ሆና ባሳደገች ልጆቿን «የሴት ልጅ»
እያለ ይሳደባል፡፡ ለመሆኑ ግን የሴት ልጅ ያልሆነ ማን አለ፡፡ «የሴት ልጅ» ማለት ስድብ ነውን? ኢየሱስ
ክርስቶስስ ቢሆን፣ መጽሐፍ ቅዱሱም ቁርአኑም እንደሚሉት ያለ አባት ከእናት አይደለም እንዴ የተወለደው? «የሴት
ልጅ» ማለት እንዴት ስድብ ይሆናል፡፡ ለመሆኑ የፈጣሪን ሥራ ተካፍላ የምትሠራ ሴት አይደለችም ወይ? ልጅን አርሞ
እና ቀጥቶ ማሳደግ የሚችለው ወንድ ብቻ ነው ያለው ማነው?
እንዲያውም አንድ ጊዜ ታናሽ ወንድሜ ነገሩ ሁሉ
አበሳጨውና «ያለ አባት ይህንን ሁሉ ለፍተሽ አሳድገሽ ለምንድን ነው በአንቺ ስም የማልጠራው? ይሄው ሰው ሁሉ
የሠራውን ሕንፃ በስሙ እየሰየመ አይደለም? ታድያ አንቺ በአካልም፣ በዕውቀትም፣ በምግ ባርም አንፀሽ ያሳደግሺውን
ልጅ በስምሽ ብትጠሪ ምን ነውር አለው? እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ የአባቴን ስም አስቀይራለሁ» ብሎ አስደንግጧት
ነበር፡፡ የርሱን ሃሳብ ለማስ ቀየር በትኁት ሰብእና እንዴት እንደ ደከመች ትዝ ይለኛል፡፡ እርሷ ልፋቱን እና
ውጤቱን እንጂ ስሙን እና ሽልማቱን መች ትፈልገዋለች፡፡
እኛን ለማሳደግ ለፋች፡፡ ቆይቶ ደግሞ ማደጋችንም
ፈተና ሆነባት፡፡ ከሦስቱ ልጆቿ ሁለታችን ወንዶች ስለነበርን ብሔራዊ ውትድርናውን ትፈራው ነበር፡፡ «ምነው ሴት ብቻ
በወለድኩ» ትላለች፡፡ በሴት ልጆች ላይ እንዲህ እና እንዲያ ዓይነት ጥቃት ደረሰ ስትባል ደግሞ፣ «እንኳንም
ወንዶች ወለድኩ» ትላለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ አምጣ እንደ ወለደችን አምጣ መልሳ ብትውጠን ትወድድ ነበር፡፡ «ምናለ
አምጬ እንደ ወለድኳችሁ አምጬ መዋጥ ብችል፤ ደኅና ዘመን ሲመጣ መልሼ እወልዳችሁ ነበር» ትለናለች፡፡
እኅቴ ሁልጊዜ አንድ ነገር ይቆጫታል፡፡ ሰው በእናቱ
ማኅፀን የኖረበት ጊዜ ለምን ከእድ ሜው ጋር እንደማይቆጠር፡፡ እንደ እናት ማኅፀን ምቹ እና ሰላማዊ፣ ያለ ሃሳብ
እና ያለ ሰቀቀን የተኖረበት የት አለ? ምርጫ፣ ቅርጫ፣ ክፍያ፣መዋጮ፣ተቆራጭ፣ ፖለቲካ፣ ፓርቲ፣ ፍርድ ቤት፣ፖሊስ
ጣቢያ፣የሌለበት ልዩ ዓለም የታለ? ታድያ እንዲህ ያለው ሕይወት ከእድሜ ካልተቆጠረ ምኑ ሊቆጠር ነው ትል ነበር፡፡
ወርቋን ሽጣ ለልጆቿ ወርቅ የሆነ ሕይወት ከለገሰች እናት በተሻለ ጀግና ሆኖ ማን ወርቅ ይሸለማል? ወርቅንማ እንደ ወርቅ በእሳት ለተፈተነ ነው መስጠት፤ ምሳሌው ከአማናዊው ጋር ሲሠምር ደስ ያሰኛልኮ፡፡
ስለዚህም እርሷን ሸልሙልኝ፤ የእኔ ጀግና እርሷ
ናት፡፡ ያለምንም በጀት፣ያለ ማንም አጋር ፣ ያለማንም አማካሪ፣ ያለ ምክር ቤት እና ካቢኔ፣ያለ ውጭ ርዳታ፣ ግብር
ሳትሰበስብ ለሠለሳ ዓመታት ያህል ቤተሰቦቿን አባትም እናትም ሆና የመራች፤ ችግርን ተቋ ቁማ ታሪክ ያደረገች እናት፣
ፓርላማ ባለበት፣ካቢኔ በሚመክርበት፣ግብር ተሰብስቦ በጀት በሚመደብበት፣የውጭ ርዳታ በሚጨመርበት፣ አማካሪ በበዛበት
ሥፍራ መምራት አትችልም የሚላት ማነው‼ የኔ ጀግና እርሷ ናት እርሷን ሸልሙልኝ፡፡
ባሎቻቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት አጥተው በብቸኛነት እና በጀግንነት ችግርን አሸንፈው፣ ልጆቻቸውን በማሳደግ ለወግ ለመዓርግ ላደረሱ እናቶች መታሰቢያ፡፡
Posted by
ዳንኤል ክብረት
No comments:
Post a Comment